በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 8 ወራት 125 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስምንት ወራት 125 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ረመዳን ዋሪዮ ገለጹ፡፡
በበጀት ዓመቱ ከገቢ ግብር 205 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ረመዳን፤ ባለፉት ስምንት ወራት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተደረገው ርብርብ 125 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ አስታውቀዋል፡፡
የገቢ ግብሩ ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ2 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አንስተዋል፡፡
ገቢው የተሰበሰበውም ከመደበኛ፣ ከማዘጋጃ ቤታዊና ከውስጥ ገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱንም በቴክኖሎጂ ማስደገፍ መቻሉን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን ማቀላጠፍና የታክስ አሥተዳደሩ በዕውቀት እንዲመራ ማስቻልም፤ ለሥራው የሚያግዝ ግብዓትና የሰው ኃይል ማፍራት አስችሏል ብለዋል፡፡
በዚህም ያለደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙ፣ ገቢን የሚደብቁ፣ ሚዛን የሚያጭበረብሩና ያለምክንያት ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች መኖራቸውም በክትትል መረጋገጡን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ከ12 ሺህ በላይ በየደረጃው የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡