Fana: At a Speed of Life!

የተመረጡ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውጤት እንዲያመጡ አምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በለውጡ ማግስት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በተመረጡ ሴክተሮች ተጨባጭ ውጤት እንዲገኝ የአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት 3ኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ መርቀው ከፍተዋል።

በዚህ ወቅትም ያልተቀየር ኢኮኖሚ የጸና ሀገር ሊያቆም አይችልም በሚል መርሕ ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ ዓላማ ከተደረገባቸው ሴክተሮች አንዱ የኢንዱስትሪው ዘርፍ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዘርፉ ካሉ ጥቅል ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የአምራች ዘርፉን ወሳኝ የኢኮኖሚ ምሰሶ ለማድረግ የ10 ዓመት የብልጽግና እቅድ ተቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡

በተለይም የግብርና ምርቶችን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲቻል ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪው የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን የሚችሉ በርካታ ማሽኖችን ሲያመርት መቆየቱንና በዚህም በርካታ ማሽኖችን መገጣጠምና ማምረት መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባውን የፍጆታ ምርት በሀገር ውስጥ መተካት መቻሏን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለአብነትም በአመት በ1 ቢሊየን ዶላር ታስገባ የነበረውን የስንዴ ምርት በራስ አቅም ማምረት መቻሉን አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም 400 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጪ ገበያ በማቅረብ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው÷ በቡና ምርት ላይ እሴት በመጨመር ረገድ አምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ሚና ነበረው ብለዋል፡፡

የማዕድን ዘርፉን ለማዘመን በተከናወኑ ተግባራት አምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ መሸጋገሪያ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በአምራች ኢንዱስትሪው አጋዥነት ማዕድን ለውጪ ገበያ ማቅረብና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ በቱሪዝም ዘርፍ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ቅርሶችን ለማደስ በተደረገው ጥረት አምራች ኢንዱስትሪው አይተኬ ሚና መጫወቱን ነው የገለፁት፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን፣ ፋይዳ እና መሶብ የመሳሰሉ ዲጂታል ሥርዓቶችን በመገንባት ረገድ የአምራች ኢንዱስትሪው እገዛ ከፍተኛ ነበር ብለዋል፡፡

እንዲሁም የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከሶስት ዓመት በፊት ከነበረበት 46 በመቶ የማምረት አቅም ወደ 61 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ሥራ ያቆሙ ፋብሪካዎች ፣ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ሥራ እንዲጀምሩና የኢንዱስትሪዎች የገበያ ድርሻ እንዲያድግ አምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.