የፖሊስን ሁለንተናዊ ብቃት ለማሳደግ እየተሰራ ነው – ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ሁለንተናዊ ብቃቱን በማሳደግ ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተናገሩ።
የ25ኛ ዙር መሰረታዊ ሰልጣኝ የፖሊስ አባላት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት፥ ተመራቂዎቹ ከ52 ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተውጣጡ መሆናቸውንና ለዘጠኝ ወራት የተለያዩ ስልጠናዎችን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ከሪፎርሙ በኋላ ባሉት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎች ማድረጉን አስታውሰው፥ በዚህም ህገ-መንግስታዊ ሥርዓትን የመጠበቅና ሰላምን የማስፈን ተልዕኮዎቹን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዛሬዎቹ ተመራቂ የፖሊስ አባላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሙያዊ ሥነምግባርን ባከበረ መልኩ እንዲተገብሩ መልዕክት ተላልፏል።
በለይኩን ዓለም