ሰመራ ከተማን በጋራ ለማልማት ያለመ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ “ሰመራ ከተማን በጋራ እናልማ“ በሚል መሪ ሐሳብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብርን አስጀምረዋል፡፡
የክልሉ ኮንስትራክሽን እና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመድ ኑር ሳሊም (ኢ/ር)፤ ሰመራ ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ እንድትሆን የ1ኛው ዙር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በክልሉ በጀት መጀመሩን እና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ ማስፈፅሚያ ተጨማሪ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የአካባቢው ተወላጆች እና ነዋሪዎች “ሰመራ ከተማን በጋራ እናልማ“ ተብሎ በተዘጋጀው መርሐ-ግብር በንቃት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ገንዘቡን በቴሌ ብር እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈቱ አካውንቶች ገቢ ማድረግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በቅርቡ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር (ቴሌቶን) እንደሚካሄድ ነው ያመላከቱት፡፡
የሰመራ-ሎግያ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አብዱ ሙሳ በበኩላቸው፤ ሰመራን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እየተከናወነ ባከለው ሥራ በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በአሊ ሹምባሕሪ