የአማራ ክልልን ሕዝብ የልማት ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልልን ሕዝብ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ በመስጠት ረገድ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መሥተዳድሩ በጎንደር የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውኃ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ሂደትን ጎብኝተዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም፤ ለበርካታ ዓመታት ተጓትቶ የቆየውን የፕሮጀክቱን ግንባታ በማፋጠን ጥቅም ላይ ለማዋል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ለበርካታ ዓመታት ሲጓተት መቆየቱን፣ ለመቆምም ተቃርቦ እንደነበረ አውስተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አመራር አሁን ላይ የግንባታ ሥራው በጥሩ አፈፃፀም ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ስር ሰዶ የቆየውን የጎንደር ከተማ የመጠጥ ውኃ ችግርን በዘላቂነት እንደሚፈታ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በክልሉ እየተካሄዱ የሚገኙትን ግዙፍ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ፍጻሜ ላይ ለማድረስ ሠላም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ሕዝቡ ለሠላሙ አጥብቆ እንዲሠራም አሳስበዋል።