አማራ ክልልን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሲቪል ሰርቫንቱ ሚና የጎላ ነው – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት የክልሉ የመንግሥት ተቋማት መሪዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እያደረጉ ነው።
አቶ አረጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት የክልሉ ሕዝብ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሶበታል።
ሆኖም ግን ሕዝቡና አመራሩ ባሳዩት አይበገሬነት በችግር ውስጥ ሆኖም ልማትን ብሎም የዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደትን ማስቀጠል መቻሉ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
በግጭት ውስጥ ሆነንም ያገኘናቸው የሰላምና የልማት ድሎች ከሕዝቡ፣ ከመንግሥት ሠራተኛውና ከአመራሩ ጥንካሬዎች የሚመነጩ መሆናቸውን ተገንዝበን ይህን ማስቀጠል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ሲቪል ሰርቫንቱና መሪዎች ሥራዎችን በውጤታማነትና በብቃት በመሥራት የሚፈለገውን ዲስፕሊን ተላብለሰው ሕዝብን የሚያገለግሉ እንዲሆኑ ጥራትን የማስጠበቅ ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ክልሉን አሁን ካለበት ዐውድ አስወጥቶ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስም የሲቪል ሰርቫንቱና መሪዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው፤ የገባንበት ችግር ከዚህ በላይ እንዳይቀጥል ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሚና መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ አሁን ካለበት በላይ ሥር የሰደደ ሰላምና የተሟላ ልማት ይፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በፖለቲካ፣ በእምነት እና በብሔር የሚታየውን ጽንፈኝነት ታግለን እስካላስተካከልን ድረስ የፈተናዎች ማራዘሚያ መሣሪያዎች ከመሆን አናመልጥም ብለዋል፡፡
ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት ውይይትን እንደ ቁልፍ ጉዳይ በመውሰድ ቀሪ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ችግሮቻችንን መፍታት ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ