እየተመናመነ ያለውን የአዞ ዝርያ የመታደግ ሥራ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ኃይቆችና ወንዞች የሚገኘው የናይል አዞ ዝርያ በቁጥርና በሥርጭት እየተመናመነ መምጣቱን ተከትሎ የአዞ ዝርያን በዘላቂነት የመጠበቅ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
በዚሁ መሠረት በጫሞ እና አባያ ኃይቆች ውስጥ የሚገኘውን በተፈጥሮው እጅግ ትልቅ የሆነ የአዞ ዝርያ በዘላቂነት የመጠበቅ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን በጋሞ ልማት ማኅበር የአርባ ምንጭ አዞ ራንች ተቋም ሥራ አስኪያጅ ዳዊት ዳኜ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የአዞ ቆዳና ሌሎች የአዞ ተረፈ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ የራንቹን አቅም ለማሳደግ እየሠሩ መሆናቸውን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
ራንቹ ከቱሪዝም መስኅብነት ባሻገር፤ በሀገሪቱ ብቸኛ የጥናትና ምርምር ማዕከል ሆኖ እያገለገለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ለ46 ሠራተኞች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አስረድተዋል፡፡
ከ30 ዓመት በላይ የሆናቸው ሁለት ትላልቅ አዞዎች፣ ከ2 እስከ 8 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 2 ሺህ 406፣ በዚህ ዓመት የተፈለፈሉ የ15 ቀን ጫጩት 1 ሺህ 815 አዞዎች በራንቹ መኖራቸን ጠቅሰዋል፡፡
በአጠቃላይ 4 ሺህ 223 አዞዎች መኖራቸውን በመግለጽ ይህም የአዞዎቹን ዝርያ ለመታደግ እየተሠራ ያለውን ሥራ ያሳያል ብለዋል፡፡
አዞዎችን በራንቹ ግቢ በማሳደግ ለእርባታ ሲደርሱ ወደ ኃይቅ እንዲገቡ በማድረግ ዝርያቸው እንዳይጠፋ ለመጠበቅ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው