ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ በተለያዩ መስኮች በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበች ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ኮንፍረንስ ቱሪዝምን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የላቀ እንቅስቃሴ በማድረግ በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበች እንደሆነ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ እንድታንሠራራ በበርካታ መስኮች ትኩረት ተሰጥቶ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ ከምንም በላይ ሰላምን ለማጽናት መንግስት የሰላም ጥሪ በማስተላለፍ ለሰላም ዝግጁ የሆኑ ታጣቂዎችን ከግማሽ መንገድ በላይ ሄዶ እየተቀበለ ነው ብለዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች ወደ ማህብረሰባቸው ተቀላቅለው ሰላማዊ ህይወትን እንዲመሩ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ እስከመጨረሻው ለቀጠለው የሰላም ጥሪ ምላሽ የማይሰጡ ታጣቂዎችን በውጤታማ የህግ ማስከበር ዘመቻዎች በማከናወን ሰላምን የማጽናት ሥራውን በከፍተኛ ውጤት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት ዋነኛው መንገድ ዘላቂ ልማት፣ ምርታማነት እና ሥራ ፈጠራን እያረጋገጡ መሄድ መሆኑን ገልጸው፤ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ፣ በርካታ ውጤቶችንም እያስመዘገበ ይገኛልም ሲሉም ገልጸዋል።
በተለይም የትኩረት መስክ ተብለው በተመረጡት የግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ኢኮኖሚ መስኮች ሰፋፊ ውጤቶች ተገኝተዋል ነው ያሉት።
በዘመን በየነ