በአማራ ክልል 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መመዝገባቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ክልሎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ባለቤት ሆነው የስራቸው አካል እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ወቅት ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ÷ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እንደ ሀገር የማህበረሰብ ትስስርን በመፍጠር የመንግሥት እና የዜጎችን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ዮዳሔ አርዓያሥላሴ በፋይዳ መታወቂያ ተደራሽነትን ከማስፋት አንጻር በቀጣይ መደረግ ስላለባቸው እና መወሰድ ስለላባቸው እርምጃዎች ምክክር አድርገዋል።
በመድረኩ የነበረውን ውይይት በተመለከተ ከፋና ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለደርሻ አካላት ዳይሬክተር ሳሚናስ ሰይፉ÷ ፋይዳ መታወቂያ ክልልን ከክልል ተቋምን ከተቋም የሚያስተሳስር በመሆኑ ከክልሎች ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል እስካሁን ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች የፋይዳ ምዝገባ ማካሄዳቸውን ገልጸው÷ በክልሉ አምስት ዋና ዋና ከተሞች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም በደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ባሕርዳር እና ጎንደር ላይ የፋይዳ ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው÷ የምዝገባ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥልና አመራሮችም በቁርጠኝት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ በርዕሰ መስተዳድሩ አቅጣጫ መሰጠቱን አመላክተዋል።
በክልሉ ባሉ መዋቅሮች እስከ ታች ድረስ በትኩረትና በቅንጅት እንዲሰራም ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።
እንደ ሀገር እስካሁን 15 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የፋይዳ ምዝገባ ማካሄዳቸውን ጠቁመው÷ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በአድማሱ አራጋው