Fana: At a Speed of Life!

የታክስ ይግባኝ ቅሬታዎችን በመመርመር ፍትሃዊ ውሳኔ እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በታክስ አከፋፈል ሒደት ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በመመርመር እና በማከራከር ነጻ፣ ገለልተኛና ፍትሃዊ ውሳኔ እየተሰጠ መሆኑን የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ሃይማኖት ደመቀ እንዳሉት÷በታክስ አከፋፈል ሒደት ላይ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች አስተማማኝና ፍትሃዊ ውሳኔ የመስጠት አቅምን ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከባለፈው ዓመት የዞሩ 326 መዝገቦችን ጨምሮ 1 ሺህ 144 የታክስ ይግባኝ ቅሬታዎች ለኮሚሽኑ መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ከቀረቡት መዛግብት ውስጥ 691 በሚሆኑት ላይ የቃል ክርክር የተደረገ ሲሆን÷ለውሳኔ በተቀጠሩት 686 መዛግብት ላይ ደግሞ ውሳኔ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

ለኮሚሽኑ በቀረቡት ቅሬታዎችም የ3 ቢሊየን 587 ሚሊየን 969 ሺህ ብር ውሳኔ ማሳለፍ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡

የውሳኔ አፈጻጸሙም 293 የጸና፣120 የተሻሻለ፣ 26 የተዘጋ፣ 232 የተሻረ እና 15 ወደ አቤቱታ አጣሪ የተመለሰ መሆኑን ሃላፊው ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል 356 መዛግብት በከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ የተጠየቀባቸው ሲሆን ÷ ከእነዚህ ውስጥም 17ቱ በድጋሚ እንዲታዩ ወደ ኮሚሽኑ መመለሳቸውን አመልክተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.