ለዘላቂ ሰላም በኮሚሽኑ የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ኮሚሽኑ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢዮጵያ እና ሲዳማ ክልሎች ከሚገኙ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከሐይማኖት አባቶች ጋር መክሯል፡፡
በዚሁ ወቅት ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፤ ባለፉት ጊዜያት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከናወኑ የምክክር ሂደቶች ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምክክር ሂደቱን ተከትሎ ማኅበረሰቡ ፊቱን ወደ ልማት በመመለስ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ እየተንቀሳቀሰ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሀገሪቱ በተጀመረው የምክክር ሂደት እየተመዘገቡ ያሉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡
የዛሬው ውይይት ዓላማም፤ የምክክር ሂደቱን ወደ ታችኛው ማኅበረሰብ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻል ነው ብለዋል፡፡