በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለኢንዱስትሪ ክላስተር አገልግሎት ከ2 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት ተዘጋጀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለላቀ አገልግሎት እና ለተቀናጀ ድጋፍ ሲባል ኢንዱስትሪዎች በክላስተር አገልግሎት የሚጠቀሙበት 2 ሺህ 310 ነጥብ 512 ሔክታር መሬት መዘጋጀቱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አባስ መሐመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት በልዩ ሁኔታ በየደረጃው ያሉ አመራሮች በአካል እየተገኙ መፍትሔ የሚሰጡበት ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡
በዚህም ባለሃብቶች በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሳተፍ በብዛት ወደ ክልሉ መግባት መጀመራቸውን ለፋና ዲጂታል አረጋግጠዋል፡፡
ለአብነትም በምሥራቅ ጉራጌ ዞን ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ አንድ የውጭ ባለሃብት 17 ሔክታር መሬት ተረክበው ወደ ሥራ መግባታቸውን አንስተዋል፡፡
በክልሉ የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን የመሠረተ ልማት ችግሮች ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት በመደረጉ ችግሮቹን በከፊል መቅረፍ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን በማስፋፋት ኢንዱስትሪዎችን እንደ የባህሪያቸው በክላስተር በማሰባሰብ የመሠረተ ልማት አቅርቦት እንዲኖር እንዲሁም የተቀናጀ ድጋፍ ለማድረግ እንዲቻል በተለያዩ ዞኖች ለክላስተር አገልግሎት የሚውል 2 ሺህ 310 ነጥብ 512 ሔክታር መሬት እንዲዘጋጅ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
በዮሐንስ ደርበው