Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ለቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት በመስጠት አዳዲስ ታሪካዊ ስፍራዎችን አልምቷል – ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት ለቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ቅርሶች እና አዳዲስ ታሪካዊ ስፍራዎች ማልማቱን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።

ሁለተኛው የቅርስ ምርምር ጉባኤ እና የአውስትሮሎፒከስ አፋራንሲስ (የሉሲ ወይም ድንቅነሽ) አጽም የተገኘበት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ተካሂዷል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒትስሯ÷ ኢትዮጵያ በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን አንስተው፤ ለቱሪዝም ዘርፍ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ ቅርሶች እና ታሪካዊ ስፍራዎች በሚገባቸው ልክ አለመልማታቸውን ገልጸዋል።

በለውጡ ማግስት መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ቅርሶች እና አዳዲስ ታሪካዊ ስፍራዎች መልማት መቻላቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ)÷ ባለስልጣኑ ላለፉት ስምንት አስርት ዓመታት በቅርስ ጥናትና ምርምር ዘርፍ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል።

በባለስልጣኑ ከሁለት ዓመት በፊት አምስት ክፍሎች ያሉት የቅርስ ጥናትና ምርምር ክንፍ ተቋቁሞ ወደ ስራ በመግባት ከበርካታ ተቋማት እና ሀገራት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከፈረንሳይ መንግስት ጋር በቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ዘርፍ በትብብር ሲሰራ መቆየቱን አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በበኩላቸው÷ የፈረንሳይ መንግስት በኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ምርምር እንዲሁም ለቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ በርካታ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በአባያ ሀይቅ፣ በኦሞ ሸለቆ እና ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ በፈረንሳይ መንግስት ድጋፍ በርካታ የአርኪዮሎጂ ጥናትና ምርምሮች መካሄዳቸውንም አንስተዋል።

በጉባኤው በእድሳት ምክንያት ለአገልግሎት ዝግ ሆኖ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.