Fana: At a Speed of Life!

የሌማት ትሩፋት ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገለጸ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ አስፋው ክፍሌ (ዶ/ር)፤ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

የቤተሰብ የምግብ ፍላጎትን የሚያሟላ እና ተጨማሪ ገቢ የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

መርሐ ግብሩ ከቤተሰብ ጀምሮ ለሀገራዊ እድገት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፤ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ በዶሮና ከብት እርባታ፣ ንብ ማነብ እና ዓሣ ልማት ባለው አማራጭ ተሳትፎ በማድረግ እራሱን ከመጥቀም አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በሀገሪቱ ያለውን የተፈጥሮ ጸጋ በአግባቡ ለይቶ በመጠቀም ረገድ ክፍተት እንዳለ ያነሱት አስፋው ክፍሌ (ዶ/ር)፤ በበጋ ስንዴ የተመዘገበው ስኬት ያለውን ጸጋ አቀናጅቶ የመጠቀም ጅምር መሆኑን ገልጸዋል።

በምግብ ራስን ከመቻል እና የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አንፃር ትልቅ ፋይዳ ያለውን የሌማት ቱሩፋትን ይበልጥ ለማሳለጥ ከቤተሰብ ጀምሮ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ለማስቀጠል ያለውን አማራጭ አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና በሌሎች ድርጅቶች ያለውን ቦታ ጥቅም ላይ በማዋል መርሐ ግብሩን በስፋት መተግበር እንደሚገባ አመልክተዋል።

በማቴዎስ ፈለቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.