በእውቀትና ሥነምግባር የታነጸ ትውልድ በመፍጠር ሂደት የመምህራን ሚና የላቀ ነው – አቶ ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል በእውቀትና ሥነምግባር የታነጸ ትውልድ በመፍጠር ሂደት የመምህራን ሚና የላቀ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
“ትውልድ በመምህር ይቀረጻል፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ ሀሳብ ከክልሉ መምህራን ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በሀዋሳ ከተማ ውይይት ተካሂዳል።
አቶ ደስታ ሌዳሞ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በትምህርት ሥርዓቱ የቆየን ስብራት ለመጠገን የመምህራን ሚና ላቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
“መምህራን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልና አዳዲስ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እየተከናወነ ባለው ስራ የወር ደምወዛቸውን ጭምር በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል” ብለዋል።
በክልልና ሀገር አቀፍ ፈተና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የእረፍት ጊዜያቸውን ጭምር በመጠቀም የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠትና መልካም ሥነምግባር የተላበሱ ተማሪዎችን ለማፍራት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ በየነ በራሳ በበኩላቸው÷ “መምህራን በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ባበረከቱት አስተዋጽኦ የተማሪዎች ውጤት መሻሻል አሳይቷል” ብለዋል።
በክልሉ የተሟላ ዕውቀትና ክህሎት ያለው፣ መልካም ሥነምግባርና ስብዕና የተላበሰ ዜጋ መፍጠር የሚቻለው ከመምህራን ጋር በቅርበት መስራት ሲቻል እንደሆነ መግለፃቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።