Fana: At a Speed of Life!

በሕክምና ባለሙያዎች የተነሱ ሐሳቦችን እንፈታለን- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሕክምና ባለሙያዎች የተነሱ ሐሳቦችን በመውሰድ ለቀጣይ ተግባራት በግብዓትነት በመጠቀም መሻሻል የሚገቧቸውን ጥያቄዎች ይፈታሉ አሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር “የላቀ የጤና አገልግሎት ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ሐሳብ የጤና  አመራሮች እና ባለሙያዎችን ያካተተ ከተማ አቀፍ የማጠቃለያ ውይይት ተካሂዷል።

የውይይት መድረኩ ዓላማ፤ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ ተግባቦት መፍጠር እንዲሁም በተፈጠረው መግባባት መሰረት የጋራ ርብርብን ለማጠናከር ነው፡፡

ከንቲባ አዳነች በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ በመዲናዋ እየተሰጠ የሚገኘውን የጤና አገልግሎት አድማስ ለማስፋት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

ለአብነትም ነባር የሕክምና ተቋማትን አቅም በማደራጀትና የነበረባቸውን የግብዓት ችግር በመፍታት 28 ነባር የሕክምና ተቋማት የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ተደርገው መዋቀራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የጤና ሴክተሩን ደረጃ በይበልጥ ለማሳደግ ብሎም ነባር የጤና ተቋማትን ለማሻሻል እና ከተማችንን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በትጋት ይሠራል ብለዋል፡፡

ለዚህም የተጀመሩ አዳዲስና ዘመናዊ የጤና ተቋማትን ግንባታ ማጠናቀቅ፣ ብቁ የጤና ባለሙያዎችን ማፍራት፣ ወቅቱ የደረሰበት ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎች ማሟላት እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሠረታዊ ሥራዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል  ነው ያሉት፡፡

በከተማ አስተዳደሩ አቅም የሚፈቱትን የትራንስፖርት አገልግሎት ፣ በማህበር ተደራጅቶ የመኖሪያ ቤት መገንባትን ፣  ነፃ የህክምና አገልግሎት፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያን መመሪያ በተሟላ ሁኔታ መተግበርን ጨምሮ አስተዳደሩ በአጭር እና በመካከለኛ ጊዜ እቅድ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡

ባለሙያዎች እያገለገሉ መጠየቅ ሲችሉ ከሙያዊ ስነ ምግባር ውጪ ስራ በማቆም ጥያቄ  ማቅረባቸው ተገቢ ያለመሆኑ ተነስቷል፡፡

ከዚህ ባለፈም በሕክምና ባለሙያዎች የተነሱ ሐሳቦችን በመውሰድ ለቀጣይ ተግባራት በግብዓትነት በመጠቀም መሻሻል የሚገቧቸውን ጥያቄዎችም በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ እንደሚፈቱ አረጋግጠዋል፡፡

በሔብሮን ዋልታው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.