አቶ ታዬ ደንደአ ጉዳያቸውን ማረሚያ ወርደው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ታዬ ደንደአ የዋስትና መብታቸው ተነስቶ ጉዳያቸውን ማረሚያ ሆነው እንዲከታተሉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አቃቤ ህግ በታዬ ደንደአ ላይ ከዚህ ቀደም አቋርጦት የነበሩ ሁለት ክሶችን ዳግም አንቀሳቅሷል።
ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251/ሐ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አቶ ታዬ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ በነበሩበት ወቅት የሀገርን፣ የመንግስትንና የህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደ ጎን በመተው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ወንጀል ሕግ አንቀፅ 257 ንዑስ አንቀጽ (ሠ) በመተላለፍ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በክሱ ላይ ተመልክቷል፡፡
በዚህም በአሽባሪነት የተሰየመው ኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም የታጠቁ ፀረሰላም ኃይሎች በአማራ ክልል ከመንግስት ጋር ጦርነት ላይ ባሉበት ጊዜ የእነዚህን ፀረሰላም ኃይሎች ፕሮፖጋንዳ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማሰብ በራሳቸው ስም በተከፈተ ማህበራዊ ሚዲያዎች የፕሮፖጋንዳ መልክቶችን ያስተላለፉ በመሆኑ ክስ ቀርቦበታል።
በሌላ በኩል የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀፅ 4/1 እና 22/13/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የተፈፀመ ህገወጥ የጦር መሳርያ ይዞ በመገኘት ክስ ቀርቦባቸው ነበር፡፡
በተጨማሪም ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታሕሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5 ሰዓት ላይ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከሁለት ክላሽ ካዝናና ከ60 ጥይት ጋር ይዘው መገኘታቸው ተጠቅሶ ክስ እንደቀረበባቸው ይታወቃል።
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ቀርቦባቸው በነበረው ሁለት ክሶች መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ተሰናብተው እንደነበር ይታወሳል።
ይሁን እንጂ በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ መያዝ ወንጀል እንዲከላከሉ ተብለው የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን በዋስ በመሆን እያሰሙ በቀጠሮ ላይ የሚገኙ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ዐቃቤ ሕግ ነፃ በተባሉበት ሁለት ክሶች የከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ በመጠየቅ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ይግባኝ ችሎት ሲከራከር ቆይቶ ትናንት ግንቦት 25/2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነሥርዓት ቁጥር 142/1/ መሰረት ነፃ የተባሉባቸውን ውሳኔዎች በመሻር ሊከላከል ይገባል ብሎ ወስኗል።
ፖሊስ በዛሬው ዕለት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሽብርና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ተከሳሹን ያቀረበ ሲሆን÷ አቃቤ ህግ ከዚህ ቀደም የተዘጉ ሁለት ክሶችን ጨምሮ መዝገቡ በፍርድ ቤቱ እንዲቀሳቀስ ጠይቋል።
ተከሳሹ አቶ ታየ ደንደአ በበኩላቸው÷ ለፍርድ ቤቱ ትናንት የተያዝኩበት መንገድ ልክ አይደለም የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎቼ ተይዘዋል፤ ከጠበቃዬ ጋር ተማክሬ መቅረብ ነበረብኝ በማለት ተከራክረዋል።
የግራና ቀኙ ክርክር የመረመረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎትም የተከሳሹ የዋስትና መብት እንዲነሳ ወስኗል።
ተከሳሹ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ትዕዛዝ በመስጠት የመከላከያ ምስክርን ለመስማት ለሰኔ 30 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሲፈን መኮንን