Fana: At a Speed of Life!

ትምህርት ላይ የገጠመውን ሥብራት ማስተካከል ይገባል- አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ትውልድን በሚቀርጹ እና ማኅበረሰብን በሚያገለግሉ መምህራን ላይ ጥቃት ሊፈጽምባቸው አይገባም አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፡፡

”ትውልድ በመምህር ይቀረጻል፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ ሐሳብ ክልላዊ የመምህራን ውይይት የማጠቃለያ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ በዚሁ ወቅት፤ መምህራን ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ፣ እንዳያስተምሩ እና መምህር ነን ለማለት እስኪሰጉ ድረስ ሲደርስባቸው የከረመውን ስጋት፣ ወከባ፣ አፈና እና ግድያ አንስተዋል።

የትምህርት ዋነኛ አቅም እና መሣሪያዎች መምህራን መሆናቸውን አስገንዝበው፤ ዘመኑ በማኅበራዊ ሚዲያ እና በስሜት በሚነዳበት ወቅት የማስተካከያ ዋናው መሣሪያ ትምህርት እና ዕውቀት ነው ብለዋል፡፡

ትውልዱ የግብረ ገብነት ችግሮች እያጋጠሙት መሆኑን አንስተው፤ ይህንን ለማስተካከልም የትምህርት ቤቶች እና መምህራንን ሚና የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

ክልሉ በትምህርት ዘርፍ የተለየ ስብራት አጋጥሞታል ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ፤ በርካታ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ማቋረጣቸውን አረጋግጠዋል፡፡

60 በመቶ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀዋል፤ ሕይወታቸውም አደጋ ተጋርጦበታል፤ ወጣቶች ለማኅበራዊ ጠንቅ ተጋልጠዋል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ሌሎች ዘርፎች ላይ የሚያጋጥም ችግርን ማስተካከል ቢቻልም ትምህርት ላይ የተደቀነው አደጋ ከፍተኛ እና ለማስተካከል አስቸጋሪ ሆኗል ነው ያሉት፡፡

መምህራን ፖለቲከኞች፤ ትምህርት ቤቶችም የፖለቲካ መድረክ አይደሉም ያሉት አቶ አረጋ፤ ትውልድን በሚቀርጹ እና ማኅበረሰብን በሚያገለግሉ መምህራን ላይ ጥቃት ሊፈጽምባቸው እንደማይገባ አስገንዝበዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.