Fana: At a Speed of Life!

አቶ አደም ፋራህ 2ኛውን የአካባቢ ብክለት መከላከል ሀገራዊ ንቅናቄ አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ 2ኛውን የአካባቢ ብክለት መከላከል ሀገራዊ ንቅናቄ በይፋ አስጀምረዋል።

አቶ አደም ፋራህ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የአካባቢ ጥበቃ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የብልጽግናችን መሰረት ነው ብለዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የዜጎች ጤና እንዲጠበቅና ማህበራዊ ኑሯቸው እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸው÷ መንግስት ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ በኮሪደር ልማት፣ በታዳሽ ኃይል አጠቃቀም ላይ በርካታ ስራዎች መስራቱን ተናግረዋል።

በንቅናቄው የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የማህበረሰብን ተሳትፎ ማጎልበት፣ የህግና ሥርዓት ተገዥነትን ማስፈን አና መልካም ለሰሩ እውቅና የመስጠት ስራዎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው÷ በዓለም ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸው÷ በኢትዮጵያ ይህንን ለመቀነስ እንዲያስችል በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን መተከላቸውን አንስተዋል።

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ የደን ሽፋን ከነበረበት የ2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 20 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አንስተው÷ በአካባቢ ጥበቃና ጽዱ ከተማ ለመፍጠር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በከተማዋ በጽዳት፣ በውሃ ፍሳሽ አወጋገድ፡ በብዙኃን ትርስንስፖርት እና በሌሎች ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች መከወናቸውንም አብራርተዋል።

በመርሐ ግብር የክልል ርእሳነ መስተዳድሮችን ጨምሮ የፌዴራልና ክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተገኝተዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.