Fana: At a Speed of Life!

አባጅፋር ያሠሩት የሁጃጆች ማረፊያ …

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሀጂ ጉዞ ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያዊው አባጅፋር ስማቸው ይነሳል። በመካ እና መዲና ለሁጃጆች ማረፊያ ይሆን ዘንድ መጠለያ እንዳሠሩ ይታወቃል።

በኢትዮ-አረብ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ በርካታ ጥናቶችን ያደረጉት የታሪክ ተመራማሪው አደም ካሚል (ፕ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ ከኢትዮጵያ የሚሄዱ ሁጃጆች ማረፊያ እንዳያጡ በማሰብ አባጅፋር በጊዜው መገበያያ የነበረውን ማሪያቴሬዛ በአቁማዳ ጭነው በመላክ መካና መዲና ላይ መሬት ገዙ፡፡

በመካ ካዕባ አጠገብ ለሁጃጆች ማረፊያ ይሆን ዘንድም ፎቅ አሰርተዋል፤ በመዲና ጊዜያዊ ቤት አስገንብተዋል፤ አባጅፋር ባስገነቡት ህንፃ እና ጊዜያዊ ቤት ኢትዮጵያን ሁጃጆች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም እረፍት ያደርጉባቸዋል።

እንደ አደም ካሚል (ፕ/ር) ገለጻ፤ በወቅቱ በሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን ችግር እንዳያጋጥማቸው በማሰብ አባጅፋር ማረፊያ ቦታም አዘጋጅተዋል።

በአሁኑ ወቅት በመካ የነበረው ሕንጻ ፈርሶ ዛይር ወደሚባል ቦታ የሄደ ቢሆንም በምትኩ እስከ 700 የሚደርሱ ምዕመናን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችል ቦታ ተሰጥቶ ለሁጃጆች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

አባጅፋር በወቅቱ ትልቅ አሻራ አስቀምጠዋል ያሉት የታሪክ ተመራማሪው፤ በወቅቱ የሀገርን ክብር ያስጠበቀ ለዛሬ የሚያኮራ ታሪክ የሆነ ሥራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በመካ መዲና ክብራቸውን በሚመጥን መልኩ በሀጅ ጉዞ ወቅት ማረፊያ እንዲያገኙ በአባጅፋር የተቋቋመ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን ግን ይህንን ታሪክ በተገቢው ልክ እንደማያውቁት የሚገልጹት የታሪክ ተመራማሪው፤ ስለሆነም ታሪኩ ለሁሉም እንዲዳረስ መጻፍ እና መነገር አለበት ብለዋል።

በመካ መዲና እንዲያገለግሉ ከኢትዮጵያ ምድር የሄዱ አገልጋዮች መሆናቸውን በመግለጽ፤ አገልጋዮቹ በመካ ብቻ ወደ 110 ፎቅ እንደነበራቸው አስታውሰዋል።

የአባ ጅፋር አሻራ የኢትዮጵያን ታሪክ ከፍ የሚያደርግ ነው በማለት ገልጸው፤ ይህንን ታሪክ በተለያየ መንገድ ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚገባ አደም ካሚል (ፕ/ር) አስገንዝበዋል።

በብርሃኑ አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.