አደገኛ ኬሚካሎችን በጥንቃቄ ለማስወገድ …
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዘንድሮው የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ አደገኛ ኬሚካሎችን በአግባቡና በጥንቃቄ ለማስወገድ በትኩረት ይሰራል አለ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ (ኢ/ር) እንዳሉት÷ አደገኛ ኬሚካሎች የአገልግሎት ጊዜያቸው ሲያልፍ በሰው፣ እንስሳት እና አካባቢ ላይ ጉዳት ሳያደርሱ በጥንቃቄ ማስወገድ ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአደገኛ ኬሚካሎች የክምችት ዳሰሳ ጥናት መከናወኑን ዋና ዳይሬክተሯ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
በዚህም የኬሚካሉ አይነት፣ የሚገኝበት ቦታ፣ የቆየበት ጊዜ እና እንዴት መወገድ አለበት የሚሉ ነጥቦች መለየታቸውን አስረድተዋል፡፡
የአደገኛ ኬሚካሎች ይወገዱልን ሪፖርቶች ሲመጡ ባለስልጣኑ በዘርፉ ባለሙያዎች በመታገዝ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል በጤና ሚኒስቴር በአዳማ፣ ሀዋሳ እና ጅማ ከተሞች በተገነቡ ማዕከላት አደገኛ ኬሚካሎችን የማስወገድ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
በእነዚህ ቦታዎች ጊዜያቸው ያለፈበቸው ኬሚካሎች፣ መድሃኒቶች እና ሌሎች አደገኛ ንጥረ ነገሮችን በአግባቡ የማስወገድ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዘንድሮው የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄም አደገኛ ኬሚካሎችን በአግባቡና በጥንቃቄ ለማስወገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ስለሆነም የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎችን ያከማቹ ተቋማት በንቅናቄው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም በሀገር አቀፍ ደረጃ አደገኛ ኬሚካሎች በጥንቃቄ የሚወገዱበት ማዕከል ለመገንባት ጥናት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ