ለቀጣይ 90 ቀናት በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሳተፍ ይገባል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀጣይ 90 ቀናት በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሳተፍ ይገባል አሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለቀጣይ 90 ቀናት በሚከናወነው የንቅናቄ አጀንዳዎች ዙሪያ ለሁሉም የከተማ አመራሮች የሥራ አቅጣጫ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት÷ ለመዲናዋ ነዋሪዎች ቀልጣፋ፣ አስተማማኝ እና ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ለዚህም በተለያየ ጊዜ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በመተግበር አዲስ አበባን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በ90 ቀናት ንቅናቄውም የከተማ ግብርናን፣ የአረንጓዴ አሻራን፣ የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎችን ለማከናወን እንዲሁም የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም 2ኛ ዙር የኮሪደር ልማትን ማጠናቀቅ፣ ገቢን ማሳደግ፣ የትላልቅ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ማፋጠን፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ፍትሃዊ አገልግሎትን ማሳለጥ ላይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
በንቅናቄው የተቃዱ ተግባራትን በስኬት ለማጠናቀቅም አመራሩ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በመንቀሳቀስ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ለዚህም ጥብቅ የድጋፍና ክትትል ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ መናገራቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የኦንላይን ሚዲያ አስተዳደር ዳይሬክተር ብሩክሰው ይልማ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ንቅናቄው ከሰኔ 5 እስከ ጳጉሜን 2017 ዓ.ም ባሉት ቀናት የሚጠናቀቅ ሲሆን÷ በዚህም 18 ዋና ዋና ተግባራት የሚከናወኑ ይሆናል፡፡
በመላኩ ገድፍ