Fana: At a Speed of Life!

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነትና የይቻላል መንፈስ ማሳያ ነው – የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነትና የይቻላል መንፈስ ማሳያ ነው አሉ።

የምዕራብ ዕዝ የሕዳሴ ኮር ሶስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል “ሕዳሴን በሕዳሴ ኮር” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ተክብሯል፡፡

በመርሐ ግብሩ የሠራዊቱ አባላት እና የአመራሮች ታላቁ የሕዳሴ ግድብን የጎበኙ ሲሆን÷ በዚህ ወቅትም የመላ ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ፕሮጀችቱ ወደ መጠናቀቅ ደረጃ በመድረሱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜ/ጄ ሙላቱ ጀልዴ እንደገለጹት÷ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወደ መጠናቀቅ ደረጃ ለመድረሱ መላው ኢትዮጵያውያን ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል።

መከላከያ ሠራዊቱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዕውን እንዲሆን የግድቡን ደህንነት ከማስጠበቅ ጀምሮ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ አስተዋጸኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በምዕራብ ዕዝ የሬጅን ሶስት ኮር ዋና አዛዥ ብ/ጄ አዘዘው መኮንን በበኩላቸው ÷ ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅና ግዳጁን በብቃት ለመወጣት ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕዳሴ ኮር የግድቡን አካባቢ ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር እያደረገ ያለውን ተግባር በውጤታማነት እየተወጣ እንደሆነ በማንሳት÷ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የሠራዊቱ መኮንኖች የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያውያን እስትንፋስ በመሆኑ ሠራዊቱ ሁሌም የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የይቻላል መንፈስ ማሳያ መሆኑን አውስው÷ ግድቡ ለሀገር በረከት የመሆን ደረጃ ላይ በመድረሱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.