Fana: At a Speed of Life!

የህንዱን የአውሮፕላን አደጋ በተንቀሳቃሽ ምስል ለዓለም ያሳየው ታዳጊ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባሳለፍነው ሳምንት መነሻውን ከህንዷ አህመዳባድ ያደረገ አውሮፕላን 242 መንገደኞችን ይዞ ወደ ለንደን ለመብረር ገና ከመነሳቱ የመከስከስ አደጋ እንዳጋጠመው ይታወሳል፡፡

በዚህም አደጋው በተከሰተበት አካባቢ የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ 270 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

አውሮፕላኑ ሲከሰከስ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል በተንቀሳቃሽ ስልኩ ቀርጾ ለዓለም ያስመለከተው ታዳጊ በወቅቱ የተመለከተውን ተናግሯል፡፡

አርያን አሳሪ የተባለው የ17 ዓመቱ ታዳጊ በመንደራቸው የአውሮፕላን ድምጽ ሲሰማ ወደ ደጅ ወጥቶ መመልከት እንደሚያዘወትር አባቱ ገልጸዋል።

አሳሪ የተባሉት የቀድሞ የሀገሪቱ ጦር አባል በስራ ምክንያት ሁለት ልጆቻቸውን እና ባለቤታቸውን ትተው ኑሯቸውን በአህመዳባድ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ካደረጉ ሶስት አመት ሆኗቸዋል፡፡

አርያን አሳሪ አባቱን ለመጠየቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አህመዳባድ በመጣበት ወቅት ነበር ይህንን የአውሮፕላን አደጋ ለማየትና ለዓለምም ለማሳየት የበቃው፡፡

እንደ ሁልጊዜው ባለፈው ሀሙስ ዕለት አውሮፕላን ለመመልከት መውጣቱንና በስልኩ እየቀረጸ በነበረበት ወቅት አውሮፕላኑ ሲከሰከስ ተመልክቷል።

አውሮፕላኑ እየተወዛወዘ ወደ ታች ሲወርድ ነበር፥ ወዲያው ሲከሰከስ በዐይኔ ተመለከትኩ በማለት በአደጋው ወቅት የተከሰተውን ሁኔታ ለቢቢሲ አስረድቷል፡፡

አርያን አውሮፕላኑ ወደ ታች እየወረደ ቢመለከትም ከሰከንዶች በኋላ አየሩ በከፍተኛ ጭስ ሲሸፈንና እሳት ሲነድ እስከሚያይ ድረስ ምን እየተፈጠረ እንደሆነ አልተገነዘበም ነበር፡፡

ለወትሮው አውሮፕላን ማየት ያስደስተው የነበረው አርያን አደጋ የደረሰበትን አውሮፕላን ከተመለከተ በኋላ ግን በጣም መረበሹንና ስልኩን መጠቀም እንደተወ አባቱ ገልጸዋል፡፡

አርያን ለጓደኞቹ ለማሳየት በስልኩ የቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምስል ዓለም አደጋውን እንዲመለከት ከማስቻሉም ባለፈ የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ ለሚደረገው ምርመራ ጠቃሚ ግብዓት አስቀርቷል።

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.