Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ለሕጻናት ሁለንተናዊ እድገት በትኩረት እየተሰራ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሕጻናት ሁለንተናዊ እድገት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው አሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

የአፍሪካ የሕጻናት ጥበቃ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

ከንቲባ አዳነች በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የአፍሪካ ሕጻናትን የወደፊት ሕይወት የተሻለ ለማድረግ መተባበር እና ትርጉም ያለው ተግባራዊ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።

ሕጻናትን ማሳደግ የአንድ ወገን ግዴታ ብቻ ሳይሆን የጋራ ሃላፊነት ነው ያሉት ከንቲባዋ÷ ነባሩን ሕጻናትን በትብብር እና በህብረት የማሳደግ አፍሪካዊ ባህል አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማስተሳሰር ይገባል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ሕጻናት በመጀመሪያዎቹ የዕድሜ ደረጃዎች ተገቢውን ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲሁም ክብር አግኝተው እያደጉ ነው የሚለውን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካ የህጻናት መብት ጥበቃ ቻርተር የቤተሰብ፣ የባህል ማንነት እና አጠቃላይ ማሕበረሰቡ የሕጻናትን ደህንነት እና እድገት ለመጠበቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው እንደሚያስቀምጥም ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የህጻናት መብት ጥበቃ ቀዳሚ ትኩረት ከሚሰጣቸው ብሔራዊ አጀንዳዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመው÷ የመጀመሪያ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነትን ማረጋገጥም ዋነኛው ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ለሕጻናት ሁለንተናዊ እድገት ትኩረት መሰጠቱን ያስረዱት ከንቲባዋ÷ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ የምገባ አገልግሎት እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ የቀዳማይ ልጅነት እድገት መርሐ ግብር ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሕጻናትን ተደራሽ እንደሚያደርግ ነው ያመላከቱት፡፡
በዚህም የሕጻናት መዋያዎችን ለማስፋፋት፣ ሁሉን አካታች የመጫዎቻ ስፍራዎችን ለመገንባት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የወላጅ የምክር አገልግሎት ባለሞያዎችን አሰልጥኖ ወደ ሥራ ለማሰማራት መቻሉን አብራርተዋል፡፡

መርሐ ግብሩ ሕጻናት ከጨቅላነት ዕድሜያቸው ጀምሮ በአካል፣ በአዕምሮ እና በሥነ ልቦና ጎልብተው እንዲያድጉ ያስችላል ማለታቸውንም የከንቲባ ጽ/ቤት ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

በመላኩ ገድፍ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.