ከፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረግ የፖለቲካ ምኅዳሩ መለወጥ አካል ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረግ የፖለቲካ ምኅዳሩ መለወጥ አካል ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ባደሩት ውይይት ላይ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።
በማብራሪያቸውም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ውይይት እኛ ውስጥ ያለውን ክፍተት ከእናንተ ስንሰማው ለመፈተሸ ስለሚያግዘን ነው ብለዋል።
የፖለቲካ ምህዳርን ማስፋት በተመለከተ ሁለት መሠረታዊ እሳቤዎች አሉን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ እነሱም ፉክክርና ትብብር ናቸው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ፉክክር ብቻ ከሆነ ወደ ግጭትና ፀብ የሚያመራና የማያግባባ ስለሚሆን መተባበር በሚገባን ጉዳይ እንተባበራለን መፎካከር በሚገባቸው ጉዳዮች ደግሞ እንፎካከራለን ብለዋል።
በፉክክርና ትብብር መካከል ሚዛንን መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸው÷ ሁሉን በፉክክር ካደረግን ውጤታማ አንሆንም ብለን እናምናለን ነው ያሉት።
አሁን ባለው የመንግስት አስተዳደር ከሚፎካከሩ ፓርቲዎች 273 ሰዎች በተለያየ ደረጃ በአመራርነት ተሳትፎ እያደረጉ እንደሆነ አንስተው፥ አራት ሚኒስትሮች፣ አራት ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም በዞንና ወረዳ መዋቅሮች በአመራርነት ተሳትፎ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ይህም መንግስት ለትብብር ቦታ እንዳለው በቂ ማሳያ ነው ብለዋል።
ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው፣ ጠንካራ ሆነው፣ ሐሳብ ኖሯቸው ከመምጣት ይልቅ በርካታ ፓርቲ እንዳለና ሁሉም የሚፈልገው ሊቀመንበርነት መሆኑና ሰብሰብ አለማለት ትብብሩን አስቸጋሪ እንዳደረገው አመላክተዋል።
ኢትጵያ አንድ ታላቅ ሀገር ሆና እንድትቀጥል በመንግስት በኩልም ሆነ በሚፎካከሩ ፓርቲዎች በኩልም በተወሰነ ደረጃ የመተው ልምምድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ከዴሞክራሲ ልምምድ ችግር የተነሳ በየቦታው ውስንነቶች ይኖራሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የሚጎድለውን እያየን እየሞላን ብንሄድ የተሻለ ይሆናል ሲሉም ነው ያስረዱት።
ብልጽግና የሆነው ሁሉ ምንም እንከን የለበትም የሚል ዓይነት ዕሳቤ እንደሌለው ገልጸው፥ እኛ ጋር ያለውን ጠቁሙን በማስረጃ እየገመገምን እርምጃ እንወስዳለን፤ እናንተም ስንጠቁማችሁ ስሙ ብለዋል።
ለመፈታተሽ ዝግጁ ካልሆናችሁ በቀር የምንፈልገውን ነገር አናመጣም የከበደንን ነገር ማወቅ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
በፉክክርና ትብብር መካከል ቆመን ምህዳር ለማነው የሚሰፋው፤ ሐሳብ አንግበውና ሰንቀው፣ ተደራጅተው፣ ሐሳቡን ሸጦ በፖለቲካ መድረክ ሚናውን ለመወጣት ለሚፈልግ ሰው ነው ወይስ ሲፈልግ ሐሳብ ሲፈልግ ነፍጥ ለሚለው ነው በማለት ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ልምምድ ከተቻለ በኮሮጆ ካልተቻለ በካልቾ ዋናው ነገር አራት ኪሎ ነው በሚል የዴሞክራሲ ምህዳርን ለመቀበል ያልተዘጋጀ ሰው ነው ያለው ብለዋል።
እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች አሁን ያለውን ዐውድ መረዳት አለባቸው፤ አሁን ያለው ሁኔታ እንደዛ አይፈቅድም ሲሉ አስገንዝበዋል።
በአድማሱ አራጋው