Fana: At a Speed of Life!

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት አምስት አመታት ሲተገበር የቆየው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በዲጂታል ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል አሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)።

የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ የሚቻለው የአሰራር ስርዓትን በኢኖቬሽን፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መደገፍ ሲቻል መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያም ወደ ዲጂታል ስርዓት መግባት የሚያስችላትን የህግ ማዕቀፍና ስትራቴጂ አዘጋጅታ ወደ ሥራ ገብታለች ብለዋል።

ወደ ዲጂታል ስርዓቱ መግባት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ተሟልተው መተግበር መጀመራቸውን አንስተዋል።

ስትራቴጂው ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ከ10 አመቱ መሪ የልማት ዕቅድ እና ከአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ጋር ተሳስሮ ሲተገበር ቆይቷል ነው ያሉት።

ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች አስመዝግቧል ያሉት በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ የስትራተጂው ትግበራ ከአንድ ወር በኋላ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

ቀጣዩ የ5 አመት ስትራቴጂ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ባለፉት አምስት አመታት የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት በመዘርጋት፣ የዲጂታል አገልግሎት በማስፋት እንዲሁም የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸው አንስተዋል።

የመንግስትን የአሰራር ስርዓት ከማዘመን ጋር በተያያዘ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን እውን ለማድረግ ከተሰሩ ስኬታማ ስራዎች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ ክልል ከተሞች በማስፋት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

https://web.facebook.com/fanabroadcasting/posts/pfbid0PtpVo8hSFpkTqZ36tqSAbq1oAjUkhFaBep2odGADHidJr25wr6k53F6yhD1CCFz1l?__cft__[0]=AZW-udAVxOAI9bwjr7hgTH8NvKjkfz21kDUWgQWf08P6xiFdMOVvOzuiDCjT4IVOtH5wMFXu4pJqWXZoKgIXrccZdPJMWgJ8Ae6-LBQ8hf7IjfMrU2Ecqjx45x1vp0L4WGz6ktUzTmlYCsXxiyd9P_Kv0NeFB6Fe6VkhqAeOPAABpWOV2Ye-JhkcRyYG0plGKbIlC3kWXMC19OtvTqREEGwX&__tn__=%2CO%2CP-R

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.