ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራትን በልማት ለማስተሳሰር በትኩረት እየሰራች ነው – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገሮች በልማት በሚተሳሰሩባቸው ሁኔታዎች ላይ እየሰራች ነው አሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሲካሔድ የቆየው የአፍሪካ የሥራ ፈጠራ ፎረም ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገሮች በልማት በሚተሳሰሩባቸው ምቹ ሁኔታዎች ላይ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች።
በተለይም የአህጉሪቱ ወጣቶች በልማት፣ በኢኮኖሚና በሥራ እድል ፈጠራ የሚቀናጁበትን ሁኔታ ማመቻቸት አንዱና ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ የሥራ ፈጠራ ፎረም የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ሀገሮች በኢኮኖሚ፣ በልማትና መሰል ተግባራት ላይ ያላቸው ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱ የአህጉሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያካሄደችው ሪፎርም እነዚህንና ሌሎች ተግባራትን ወጥ በሆነ መልኩ ለማከናወን እንዳስቻላት አስታውቀዋል።
በተለይም አምስት የኢኮኖሚ ልማት ምሰሶዎችን በመለየት እያከናወነች ባለው ተግባር አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡