መጪው ምርጫ የትብብርና ፉክክር ባህል የሚገነባበት እንዲሆን በትኩረት ይሰራል – አቶ ፍቃዱ ተሰማ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ መጪው ምርጫ የትብብርና ፉክክር የዴሞክራሲ ባህል የሚገነባበት እንዲሆን በትኩረት ይሰራል አሉ።
በጎንደር ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ የፓርቲው የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊዎች የተሳተፉበት የግምገማ መድረክ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቅቋል።
አቶ ፍቃዱ ተሰማ የመድረኩን ማጠቃለያ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ፓርቲው መጪው ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን መላ አባላቱን የማዘጋጀት ሥራዎችን በትኩረት ያከናውናል ብለዋል።
ለዚህም የአባላት የሥነ ምግባር ደንቦችን በማዘጋጀት በምርጫው የትብብርና ፉክክር ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
አባላቱ በፓርቲው እሳቤዎች፣ መተዳደሪያ ደንብና አሰራሮች ዙሪያ ወጥና የተቀራረበ ግንዛቤ በመያዝ ተቋማዊ ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ የአቅም ግንባታ ይሰጣል ነው ያሉት።
የፓርቲው አደረጃጀቶች በልማት፣ በሠላምና በመልካም አስተዳደር ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስቀጠል እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።
የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደ ፓርቲና መንግስት ሰፋ ያሉ ውጤቶች የተመዘገቡበትና የማንሰራራት ዘመን በተጨባጭ የታየበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ዓመቱ በፓርቲው ውስጥ የአመለካከት፣ የተግባር አንድነትና ህብረ ብሔራዊነት የተጠናከረበት እንደነበረ ማንሳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ከተረጂነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት በጎ ጅምር የታየበት፣ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ የሀገሪቱን በጀት በትሪሊዮን እንዲጸድቅ ያስቻለና የዕዳ ቅነሳ የተደረገበት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራና የከተሞች ኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ውጤታማ እንደነበር አብራርተዋል፡፡
በሠላም ማስከበር ሂደቱ የታጠቁ ኃይሎች የመንግስትን የሠላም አማራጭ ተቀብለው ተሃድሶ በመውሰድ በስፋት ወደ ሠላማዊ ህይወት መመለሳቸውን አስታውሰዋል።
በቀጣይም ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ ፓርቲው የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም ኃላፊው አረጋግጠዋል።