የቡና ልማት ውጤትን በማስቀጠል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ በቡና ልማት የተገኘውን ውጤት በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይሰራል አሉ።
በክልሉ የቡና ልማት የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ መድረክ ዛሬ በአዳማ ተካሂዷል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመድረኩ ተገኝተው እንዳመለከቱት፤ ቡና ለብልጽግና ጉዞ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በክልሉ የቡና ልማትን ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት አመርቂ ውጤት ታይቷል ብለዋል።
በተለይም የቡና ምርትና ጥራትን በማሻሻል በዓለም ገበያ ያለውን ተወዳዳሪነት የበለጠ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግሩን እውን ለማድረግ በልዩ ትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል።
በዚህም መንግስት፣ አርሶ አደሮች፣ ቡና ላኪዎችና ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ በምርትማነትና በገቢ የተሻለ ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት።
ቡና ላኪዎች ለአርሶ አደሩ የተሻለ ተጠቃሚነት ድጋፋቸውን ከማጠናከር ባሻገር በቡና ልማት በስፋት እንዲሳተፉ ጠይቀው፤ የክልሉ መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በቡና ልማት ከፍተኛ ውጤት እየታየ በመምጣቱ ከቡና ምርት ወጪ ንግድ ከፍተኛ ገቢ እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
የተመዘገበው ውጤት ከሁሉም ክልሎች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት በመሰራቱ እንደሆነ አመላክተዋል።
የቡና ወጪ ንግድ ሥራ ለዘመናት በተወሰኑ ላኪዎች እጅ እንደነበረ አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩን ጨምሮ አዳዲስ ላኪዎች እንዲካተቱ አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው 469 ሺህ ቶን ቡና 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፤ በ2018 በጀት ዓመት 600 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል።