በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ1 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ተሰራጨ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ1 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ መኮንን ጋሶ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለፁት÷ በመኸር ወቅት ሆርቲካልቸርን ጨምሮ በዋና ዋና ሰብሎች 489 ሺህ 500 ሄክታር ማሣ በማልማት ከ28 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።
ለዚህም ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን ጠቅሰው÷ እስካሁን ከ1 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል ብለዋል።
ከባለፉት ዓመታት አንጻር ዘንድሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተሻለ ትብብር በመሰራቱ የአፈር ማዳበሪያው በወቅቱ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀሪው ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው የአፈር ማዳበሪያ የዘር ወቅት ሳያልፍ ለአርሶ አደሩ በፍጥነት እንደሚሰራጭ አረጋግጠዋል።
ህገ ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ግብይትን ለመከላከል ክትትል በማድረግ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በዚህም ህገ ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ግብይት እንቅስቃሴን ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ