በክልሉ የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት ለማሻሻል በተቋም ግንባታ ላይ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቀልጣፋ የፍርድ አገልግሎት መስጠት የሚችል ተቋም ለመገንባት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፡፡
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ተቋም ለመገንባት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
በዚሁም በበጀት ዓመቱ የሰው ኃይልን ከማጠናከር አንፃር ከ20 በላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች መቀጠራቸውን ጠቁመዋል።
ፍርድ ቤቶቹን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ከጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከ ወረዳ ፍርድ ቤት ድረስ የቪዲዮ ኮንፍረንስ ማድረግ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ስርዓት መዘርጋቱንም አንስተዋል።
በተጨማሪም አስፈላጊ የሆኑ የቢሮ ቁሳቁስ የማሟላት ስራዎች መከናወናቸውን አንስተው÷ የኔትወርክ እና ዳታ ቤዝ አስተዳደር እንዲሁም የጥገና አግልገሎት ተቋሙ ራሱን ችሎ እንዲያከናውን ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ደንበኞች ጉዳያቸውን በመመልከት የመረጃ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ተች ስክሪን በተቋሙ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉም ጠቁመዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት በክልሉ የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ የመስጠት አቅም ለማጎልበት በሰው ኃይል እና ቴክኖሎጂ የማዘመን ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ