Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል 29 ሚሊየን መጻሕፍትን ለማሳተም እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በሚቀጥለው ዓመት 29 ሚሊየን መጻሕፍትን ለማሳተም እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በ6ኛው ጨፌ ኦሮሚያ 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤ የትምህርት ዘርፉን ለማጠናከር የተከናወኑ ተግበራትን በተመለከተ ከጨፌው አባላት ለተኑሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በምላሻቸውም በክልሉ የትምህርት ዘርፉን ለማጠናከር፣ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ  እና የተማሪዎች መማሪያ መጻሕፍትን ተደራሽ ለማድረግ መንግስት በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል፡፡

በተለይም ከመጽሐፍ ተደራሽነት አንፃር በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት 29 ሚሊየን መጻሕፍትን ለማሳተም እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የመምህራን እጥረትን ለመፍታትም ከ4 ሺህ በላይ መምህራን እንደሚቀጠሩና ለ100 ሺህ መምህራን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው÷ ከጨፌ ኦሮሚያ አባላት የግብርናውን ዘርፍ በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም በክልሉ የአፈር ማዳበርያ ለአርሶ አደሩ በፍጥነት እንዲደርስ በተደረገው ጥረት እስከ አሁን 5 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ማከፋፈል መቻሉን ጠቁመዋል።

የሚያስፈልጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው ያሉት ኃላፊው÷ ትራክተር እና ሌሎች የግብርና ማሽነሪዎች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ነፃነት ወርቅነህ (ፕ/ር) በክልል በጤናው ዘርፍ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት የተሻለ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የጨፌው አባላት በሰጡት አስተያየት በክልሉ በ2017 ዓ.ም የተሰሩ ስራዎች እውን እንዲሆኑ መንግስት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው÷ የማህበረሰቡም ተሳትፎ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

የመሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አንስተው÷ ለትምህርት ጥራት፣ ለጤና አገልግሎት ተደራሽነት፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ለማስፋፋት እና ዘላቂ ሰላምን ይበልጥ ማስፋት በቀጣይ ሊሰሩ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆኑን አመላክተዋል።

በታምራት ደለሊ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.