በአስማሚነት መር ዳኝነት 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ግምት ያላቸው ጉዳዮች በእርቅ እልባት አገኙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ከቀረቡለት መዛግብት ውስጥ በአስማሚነት መር የዳኝነት አገልግሎት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ጉዳዮች በእርቅ እልባት አግኝተዋል አለ፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ሌሊሴ ደሳለኝ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ በ2017 በጀት ዓመት 547 የአስማሚነት መር የዳኝነት አገልግሎት መዝገቦች ለፍርድ ቤቱ ቀርበዋል፡፡
መዝገቦችም የቀጥታ ክስ፣ የንግድ እና የኮንስትራክሽን ጉዳዮች እንዲሁም የውልና ከውል ውጪ ያሉ ክርክሮች ናቸው፡፡
ከእነዚህ ውስጥም 9 ነጥብ 14 ከመቶ የሚሆኑት መዛግብቶች በእርቅ ስምምነት መጠናቀቃቸውን ጠቁመው ÷ ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ግምት እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡
497 መዛግብቶች ባለጉዳዮች ለመስማማት ፍላጎት የሌላቸው በመሆኑ ስምምነት ያልተደረሰባቸውና በድጋሚ ለመደበኛው ችሎት መመራታቸውን ጠቁመዋል።
በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች በተከራካሪ ወገኖች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በስምምነት መፍታት ለፍትሕ ሥርዓቱ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
አስማሚዎች መብቶቻቸውንና ኃላፊነቶቻቸውን ተረድተው የማስማማት ተግባራቸውን በጥራት፣ በብቃትና ምክንያታዊ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያከናውኑም ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በታሪክ አዱኛ