Fana: At a Speed of Life!

ጋሽ ነብይ – በፓሪስ ዋሻ ምን ገጠመው?

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፈረንሳይ ምስራቅ ፓሪስ አንድ እድሜ ጠገብ ዋሻ ውስጥ፡፡ ዕይታን ከሚፈትነው ጨለማ ድንግዝግዝ የብርሃን ፍንጣቂዎች ጎልተው ለመውጣት ይታገላሉ፡፡

አስፈሪ ድባብ ባለው የዋሻው ሆድ ውስጥ፤ ሦስት ለምድር ለሰማይ የከበዱና ፍፁም ጥቁር ቀለም ያለው ካባ የደረቡ ዳኞች መሰየማቸው ግርታን ፈጥሯል፡፡

ነፍስ ለፍርድ የቀረበችበት ቅፅበት በመስለው ዋሻ፣ ከአራቱም ማዕዘናት የተጠሩት ታዳሚያን ቀጥሎ የሚሆነውን መለየት አልያም መገመት ቸግሯቸው ተስተዋሉ፡፡

ገሚሱ በጉጉት ቀሪው በጭንቅት ቀጣዩን ክስተት በሚጠብቁበት መቼት ያን ጥቁር ካባ ከደረቡት፤ የመካከለኛው ዳኛ ድንገትን ወንበሩን ሳቡ፡፡

የወንበሩ እግሮች ከወለሉ ጋር በፈጠሩት ፍትጊያ መጠነኛ ድምጽ ማሰማቱ የዋሻውን ድባብ ለመረዳት ሁነኛ አጋጣሚ ሆነ።

በረጅም ቁመና፣ ፈርጣማ እና የተደላደለ ሰውነት ላይ ጥቁሩን ካባ የደረቡት ዳኛ ዘለግ ባለ፡ ግን ደግሞ በጎርናና ድምጽ የአንድን ሰው ስም ጠሩ፡፡ ይሄኔ ቀጣዩ ታሪክ ለንግርት እንዲበቃ መነሾ ሆነ፡፡

ለወትሮው በሚሊየን ጎብኝዎች ናፍቆትና ትዝታ ጥላ የምታልፈው … መች ይሆን የማይሽ? የሚባልላት ፓሪስ፤ ይመጣ ይሆን? ብላ የምትጠብቀው እንግዳ ጠርታ ትንቆራጠጥ ይዛለች፡፡

ሁለት ምዕተ ዓመት የሞላው የፈረንሳይ የደራሲያን እና የሙዚቃ አቀናባሪዎች ማኅበር የፓሪስ ጭንቀት ምክንያት ነበር፡፡

ማህበሩ ቀን ቆርጦ ቦታ መርጦ ላሰናዳው የኪን ድግስ ሁነኛ ጠቢባን ከምድሪቱ እንዲታደሙ በሞቴ ብሎ ጠርቷል፡፡

የክብር ጥሪው ”እኔ ግን ገጣሚ ነኝ” ለሚለው ሆኖም የባለጉዳይ የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ ጸሐፌ ተውኔት፣ ተዋናይና ጋዜጠኛዉ ጋሽ ነብይ መኮንን በኩል ወደ እናት ሀገር አትዮጵያ መጣ።

እናም ብዙዎች በሴን ወንዝ ጀልባ ቀዘፍን፣ በጎዳናዎች ሽር አልን፣ ኤፍል ማማን በካሜራ አስቀረን፣ የሉቨራ መዘክርን ከትዝታችን ማህደር ከተትነው፣ በኖተርዳም ካቴድራል ኤሎሄ አልን ሲሉ ብዙ የሚያወሩላት ፓሪስ በተራዋ ይመጣ ይሆን? ስትል የምጠብቀው እንግዳ ገጥሟታል፡፡

ጠሪ አክባሪ ነውና፤ የኛ ሰው በአሜሪካ የጉዞ ማስተዋሻ ጸሐፊው፣ የናትናኤል ጠቢቡና ጁሊየስ ቄሳር ተርጓሚው፣ ሐሳብ ከፊደሉም ከወረቀቱም የሚዋደድለት ነብይ ወደ ፈረንሳይ አቀና፡፡

አክብራ ጠርታው አክብሯት በመናገሻዋ ተገኝቷልና ፓሪስ ነብይን በቀጥታ ወደ ሰሜናዊ ክፍሏ ወሰደችው፡፡ በዚያም ሁለት ምዕተ ዓመት ያስቆጠርው የፈረንሳይ የደራሲያንና እና የሙዚቃ አቀናባሪዎች ማኅበር ድግሱን አሰናድቷል፡፡

የኪነ ጥበብ ድግሱ በዘመነኛ አዳራሾች ሳይሆን ዘመናትን በሚዘክር በአንድ ጥንታዊ ዋሻ ውስጥ መከወኑ ለጋሽ ነብይ እንግዳ ስሜትን ከአግራሞት ጋር መጫሩ አልቀረም፡፡

ነብይ ወደዋሻው ሲዘልቅ ከጨለማ ጋር መጋፈጥ ነበረበት፤ እድሜ ጠገቡ ዋሻ ፍፁም ፅልመት ውስጥ ነው ከመባል ያዳነው በጥንቃቄ ጭላንጭል ብርሃን ኢንዲፈነጥቁ በተደረጉ ደካማ የብርሀን መስመሮች ነበር፡፡

በዚህ ድባብ ውስጥ እንደጋሽ ነብይ ሁሉ የምድሪቱ ድንቅ ከያኒያን ታድመዋል፡፡ ሆኖም ማን የቱ ጋር እንደሆነ መለየት አዳጋች ነበር፡፡

ፍፁም ሩቅ ከሆነ ስፍራ የተከፈተ የሚመስል፤ ግን ደግሞ ወደ ላቀ መመሰጥ የሚያሻግር የቫዮሊን ክሮች ግርፍ እንደምንጭ ውኃ ይንቆረቆራል፡፡

ድንገት አንዱ ግጥም ማንበብ ጀመረ፤ ሌላኛው ቀጠለ፤ ከወዲያኛው ጥግ አንዷ ሰለሰች ግርምታ፣ አድናቆት፣ ተመስጦ፣ ሳቅ፣ ቁጭት፣ ጭብጨባ ሁሉም ስሜቶች በየተራ ይፈራረቁ ጀመር፡፡

በዚህ መሀል አንድ ሰው ወደ ጋሽ ነብይ ጠጋ ብሎ … ”አንድ ግጥም አልያዝክም?” አለው
ጋሽ ነብይ … ማ ! እኔ?
ሰውየው … አዎ.. እጅህ ላይ አንድ ግጥም የለም?
ጋሽ ነብይ … አይ እኔ የምፅፈው በአማርኛ ቋንቋ ነው እኔ ብኮራበትም ለእናንተ ትረዱት ዘንድ አይቻላችሁማ!
ሰውየው … ግዴለህም ግጥም ቋንቋ አይደለም ዜማ ነው የሰለጠነ ጆሮ አለን
ጋሽ ነብይ … እረ … እንዴዴዴ … የሰለጠነ ጆሮ?
ሰውየው … ጋሽ ነብይን በአክብሮት ጭላንጭል ብርሃኗ ጎላ ወዳለችው ስፍራ ወሰደው፡፡

ጋሽ ነብይ በክብር ሊታደም በተጋበዘብት መድረክ ላይ ድንገት እራሱን ግጥም አቅራቢ ሆኖ አገኘው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ምሩቅ፤ ግን የስነ ጽሑፍ ጠቢብ፣ የ90ቹ የእነ ማፍቀር ነው መሰልጠን እና ትርፉ መዘዝ አለው ማኅበራዊ ጉዳይን የነቀሱ፤ የእይታ ብርሃን የፈነጠቁ የሙዚቃ ግጥሞች ገጣሚ፣ የስውር ስፌት እና ጥቁር ነጭ፣ ግራጫ የስነ ግጥም መድብሎች ከታቢ፣ ‘ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ’ ረጅም ልቦለድን ‘ነገም ሌላ ቀን ነው’ ሲል በአማርኛ ያስነበበን ጋሽ ነብይ “ሜዲትራኒያ” ሲል ፈረንጂኛ ቋንቋ በነገሰበት ዋሻ ውስጥ በአማርኛ ግጥም ያነብ ጀመር ….

“ሜዲትራኒያ”
ሜዲትራኒያ የባሕር መቀነት
ዞርኩት
እሱም ዞረኝ
ውስጤንም ዞሮ አየኝ
ጠብ አይልም ካንጀት!
እኔም በቃኝ አላልኩ
እሱም ማማር አይተው
የዝንተ ዓለም ውበት ….
የዘለዓለም ሽታ…
የዕርጋታ አየር ጣዕም…
የእፎይታም እስትንፋስ …
የት ነው መጨረሻው?
እራሱ ውስጥ ነው?
ወይ ሌላ ማብቂያ አለው?
እትብቱ ጠፋብኝ ብዞረው ብዞረው፡፡
ያውቅ ይሆን ቀይ ባሕር
የኔው ሀገር ውኃ
…. ሄጄ ብጠይቀው?
ሜዲትራኒያ
ጅምሩ አይታይም
ፍፃሜውም ሩቅ ነው፡፡
ይህ የውበት አድማስ … እንደኔው ልብ ነው…
ይጠልቃል…
ይርቃል…
እንደውኃ መንጭቶ ህዋ ሆኖ ያልቃል
… እንደኔው ልብ ነው …
ጥር 11/1984
[ለማይለካ ልብ]
ከካን ወደ ቱሉ ጉዞ — ደቡብ ፈረንሳይ
ጋሽ ነብይ ግጥሙን በቃሉ ሲወጣው፤ ጣሊያናዊ ሰዓሊ ዜማውን እየተከተለ ግጥምን በቅርፅ በማስፈር ዘዴ (Engraving) ይስል ነበር፡፡

ይሄኔ ዋሻው በብርሃን ተሞላ፣ ለመለየት ያዳግቱ የነበሩ ስመጥር ከያኒያን በዋሻው ታዩ፡፡ ሙዚቃ በተራዋ ነገሰች፡፡ ወይኑ ተቀዳ፣ ሻምፓኝ ተረጨ፡፡

በዚህ መሃል ያ ጣሊያናዊው ሰአሊ የጋሽ ነብይ ግጥም ወደ እንግሊዘኛ ተተርጉሞ እንዲሰጠው ጠየቀ፡፡ ጋሽ ነብይም ወዲያው ይህን አደረገ፡፡

ከዕረፍት መልስ፤ ድንገት ካባ የደረቡ ሦስት ሰዎች ወደ መድረክ ወጡ፡፡ ፀጥታም ሆነ፡፡ ገጣሚና ጋዜጠኛው ነብይ ደግሞ ምን ይሆን? አለ፡፡ ከዚያም ከሦሶስቱ ዳኞች አንደኛው ብድግ አለ፤ ግራ ቀኙንም በጥሞ እና በመርማሪ ዓይን አየ … አስከትሎም የዚህ ታሪካዊ ሁነት የግጥም ውድድር አሸናፊው ገጣሚ ነብይ መኮንን ከኢትዮጵያ! አለ፡፡

ዋሻው በላቀ የአድናቆት ጭብጨባ ተናጠ… ገሚሱ ጋሼን እንኳን ደስ ያለህ ለማለት ተጣደፈ… ታላቅ ደስታም ሆነ!

ጋሽ ነብይ በመድረኩ እናት ሀገሩን በራሱ ቋንቋ፤ ቀለምና ወዘና ከፍ አደረገ፡፡

ኢትዮጵያዊያን እንኳንስ አስበው አልመው ይቅርና ድንገት በተገኙበት መድረክ ማሸነፍ መለያቸው እንደሆነም አስመሰከረበት፡፡

የገንዘብ ሽልማት ቀጠል፡፡ ግጥሙ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተተርጉሞ እንዲሰራጭ ተፈቀደ፡፡ ነብይ በአምስት የአውሮፓ ሀገራት የግጥም እና የስዕል ዐውደ ርዕይ የማዘጋጀት እድል ተመቻቸ፡፡

ጋሽ ነብይ ለሽልማት በወጣበት ቅፅበት እንደሀገር ልሳነ ብዙ መሆናችንን ደሰኮረ፡፡ በአንድ ድንጋይ … እንዲሉ ስለ አማርኛ ቋንቋና ፊደላቱ መጠነኛ ማብራሪያ በመስጠት የባሕል ዲፕማሎሲ ከወነበት፡፡

ይህ ከሆነ ከጊዚያት በኋላ ከዕለታት በአንደኛውም ቀን አዲስ አበባ ውስጥ፡፡ ከፈረንሳይ የመጣ ሰው ይፈልጋሀል ተብሎ ጋሽ ነብይ ወደ ቀጠሮው ቦታ አመራ፡፡ ያኔ ግጥሙን ወደ ስዕል ይቀይር የነበረ ጣሊያናዊ ሰአሊ፤ ግጥሙንም በኢንግሪቪንግ ዘዴ የተሳለውንም ስዕል ይዞት መጥቶ ኖሮ በክብር ለጋሸ ነብይ አበረከተ፡፡ እንደገና መገረም! እንደገና መደነቅ! የጋሽ ነብይ መኮንን የስሜት መዳረሻዎች ሆኑ፡፡
የዚህ ታሪክ ከታቢ የሁለገቧን ከያኒ አዳነች ወልደገብርኤልን የ90ቹ የጠብታ ዕትም ዋቢ አድርጓል፡፡

በአስማረ ቸኮል

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.