የሳይንስ ሙዚየም አፍሪካ ቴክኖሎጂ እየፈነጠቀባት ስለመሆኗ ማሳያ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም አፍሪካ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት በራሷ መንገድ በመቀየስ የተስፋ ጎህ እየፈነጠቀባት የምትገኝ ስለመሆኗ አንዱ ማሳያ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዛሬ ከኩባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆርጌ ሉዊስ ታፒያ ፎንሴካ ጋር በመሆን የሳይንስ ሙዚየምን ጎብኝተናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም አፍሪካ የኋላቅርነት ትርክትን የሚቀይር መሆኑን ገልጸው፤ ሙዚየሙ አፍሪካ ዓለም የደረሰበትን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት በራሷ መንገድ በመቀየስ የተስፋ ጎህ እየፈነጠቀባት የምትገኝ አህጉር ስለመሆኗ አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሙዚየሙ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች የፈጠራ ህልሞቻችውን እውን እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን የኩባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆርጌ ሉዊስ ገልጸውልኛል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂው መስክ አሁን ያለችበትንና ልትደርስበት የተለመችውን ራዕይ የሚያሳይ መሆኑን እንዳነሱላቸው አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ እና ኩባ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ጉዳዮች ዙሪያ ትብብራቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጋራ ለመስራት መግባባታቸውንም ጠቁመዋል።