የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን እያገኙ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን እያገኙ ነው አለ በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት።
በኢኒስቲትዩቱ የትንበያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ከሰኔ ወር ጀምሮ እስካሁን የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን እያገኙ ይገኛል።
በዚህም 224 የሚደርሱ አካባቢዎች በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር እስከ 127 ሚሊ ሜትር የሚደርስ እጅግ ከባድ የዝናብ መጠን እና ስርጭት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
ይህም ለግብርና ስራዎች እና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሂደ ለሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው÷ በሚቀጥሉት 10 ቀናት ለዝናብ መፈጠር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የአየር ሁኔታ ክስተቶች እየተጠናከሩ እንደሚመጡ ተናግረዋል።
የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ የዝናብ መጠን እና ስርጭት እንደሚኖራቸው ጠቁመው÷ ይህም ቀሪ የግብርና ስራዎችን ለማከናወን ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ አመላክተዋል።
በዚህም በምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን እና መካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የአሀዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ነው ያሉት።
በተጨማሪም በሰሜን ምስራቅ እና ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖረው የዝናብ ስርጭት አስቀድሞ በምዕራብ እና የደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀደም ብሎ እንደሚጀምርና በሂደት ወደ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን እና ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደሚስፋፋ አንስተዋል።
በመሆኑም የሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመደበኛ ሁኔታ ዝናብ ማግኘት የሚጀምሩት ከሐምሌ አጋማሽ በኋላ እንደሆነ በማንሳት አሁን ላይ በምስራቅ አማራ እንደ መርሳ፣ ሮቢት፣ ወልድያ፣ ሐራ፣ ጎብዬ አካባቢዎች ባለፉት ቀናት እስከ 24 ሚሊ ሜትር የሚደርስ የዝናብ ስርጭት መጠን ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በመጪዎቹ ቀናትም በእነዚህ አካባቢዎች የተጠናከረ የደመና ሽፋን እንደሚኖራቸው አንስተው÷ በምስራቅ አማራ፣ ደቡብ እና ምስራቅ ትግራይ፣ አፋር ክልል ለመኸር እርሻ ስራዎች የሚያግዝ ጥሩ እና በቂ የሆነ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸውም ነው ያብራሩት።
በዮናስ ጌትነት