Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ የማድሪድ 10 ቁጥር ማልያ ለባሽ ኪሊያን ምባፔ…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሪያል ማድሪድን ማልያ በመልበስ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው ኮከብ አሁን የልጅነት ሕልሙ ለነበረው ክለብ መጫወት ብቻ ሳይሆን በክለቡ ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን 10 ቁጥር ማልያ ለብሶ የመጫወት ዕድል አግኝቷል፡፡

ገና ታዳጊ እያለ ለሪያል ማድሪድ የመጫወት ሕልም የነበረው ፈረንሳዊው ኮከብ ኪሊያን ምባፔ በልጅነቱ የሚወደውን ክለብ የሎስብላንኮቹን ማልያ እየለበሰ አድጓል።

በስፔኑ ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ ቤት ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው የማልያ ቁጥሮች መካከል 7 እና 10 ቀዳሚዎቹ ናቸው።

ፈረንሳዊው የፊት መስመር ተጫዋች ኪሊያን ምባፔ በሪያል ማድሪድ ትልቅ ከሚሰጣቸው እና ትልልቅ ተጫዋቾች ለብሰውት የተጫወቱበትን 10 ቁጥር ማልያ ተረክቧል።

ኪሊያን ምባፔ በቀጣይ በብሔራዊ ቡድን ሆነ በክለብ የውድድር መርሐ ግብሮች 10 ቁጥር ማልያን ለብሶ የሚጫወት ይሆናል።

ከዚህ ቀደም በሪያል ማድሪድ 10 ቁጥር ማልያን ለብሰው የተጫወቱ ተጫዋቾች በክለቡ በነበራቸው ቆይታ የራሳቸውን ደማቅ ታሪክ ሰርተው ማለፋቸው አይዘነጋም።

ከራይሞንድ ኮፓ እስከ ፑሽካሽ፣ ከክላረንስ ሲዶርፍ እስከ ሉዊስ ፊጎ፣ ከሽናይደር እስከ ሮቢኒሆ፣ ከሜሱት ኦዚል እስከ ሉካ ሞድሪች ያሉ ከዋክብቶች በነጮቹ ቤት በ10 ቁጥር ማልያ ደምቀው ካለፉት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።

የክሮሺያዊውን የመሃል ሜዳ ኮከብ ሉካ ሞድሪች ሪያል ማድሪድን መልቀቅ ተከትሎ የተለያዩ ተጫዋቾች ይህንን ማልያ የመውሰድ ፍላጎት ቢኖራቸውም ክለቡ ለኪሊያን ምባፔ አስረክቧል።

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከ13 ዓመታት ቆይታ በኋላ ከሎስብላንኮቹ ጋር የተለያየው እና 10 ቁጥር ማልያን ለብሰው ካለፉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሉካ ሞድሪች ሪያል ማድሪድ አዲሱ 10 ቁጥር ለባሽ ኪሊያን ምባፔ መሆኑን ሲያሳውቅ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ለኪሊያን ምባፔ ድጋፉን አሳይቷል።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ከዋክብቶች ታሪክ የሰሩበትንና እሱን በልጅነቱ ለብሶት የታየውን ይህንን 10 ቁጥር ማልያ ለብሶ ኪሊያን ምባፔን በአዲሱ የውድድር ዘመን እንመለከተዋለን።

ኪሊያን ምባፔ ሪያል ማድሪድን ሲቀላቀል ከሀገሩ ልጅ ካሪም ቤንዜማ 9 ቁጥር ማልያን ተረክቦ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ተመልክተነዋል።

ፈረንሳዊው ኮከብ ልክ እንደ ብሔራዊ ቡድኑ ሁሉ አሁን በሪያል ማድሪድ ቤት 10 ቁጥር ማልያን ለብሶ ይጫወታል።

ኪሊያን ምባፔ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በግሉ ምርጥ ብቃቱን በማሳየት ግቦችን ቢያስቆጥርም ከማድሪድ ጋር በዋንጫ የታጀበ ጊዜ ማሳለፍ አልቻለም፡፡

በአዲሱ የውድድር ዓመት በዚህ ማልያ በሪያል ማድሪድ ከዋንጫ ጋር ይገናኝ ይሆን የሚለው ተጠባቂ ነው፡፡

በሎስብላንኮቹ ቤት ትልልቅ ከዋክብቶች በርካታ ታሪክ የሰሩበትን ማልያ ለብሶ የመጫወት ዕድል ያገኘው ኪሊያን ምባፔ በቆይታው በዚህ ማልያ የራሱን አሻራ ያሳርፋል ተብሎ ይጠበቃል።

በወንድማገኝ ፀጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.