በሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ወንጀል ተግባር የተሰማሩ 138 ተጠሪጣሪዎች ባንክ ሒሳብ ታገደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ተግባር ላይ የተሰማሩ 138 ተጠርጣሪዎች የባንክ ሒሳብ ታግዷል አለ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፡፡
አገልግሎቱ ሕጋዊና መደበኛ የባንክ ሥርዓትን ወደ ጎን በመተው በሕገ ወጥ እና ትይዩ ገበያ የውጭ ምንዛሪ ወንጀል ላይ የተሰማሩ 138 ዋነኛ ተጠርጣሪዎች የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲታገድ መደረጉን አመልክቷል፡፡
የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት በሕጋዊና መደበኛ የባንክ ሥርዓት በኩል እንዲከናወን በግልጽ የተቀመጠ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
ስለሆነም በሕገ ወጥ መንገድ የምንዛሪ አገልግሎት የተሰማሩት ላይ ጠንካራ የሕግ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን ነው ያስገነዘበው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በወንጀል ድርጊቱ ላይ ተሰማርቶ መገኘት የንብረት መወረስን ጨምሮ በከፍተኛ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ መደበኛ የባንክ ስርዓትን እንዲጠቀም በመንግስት በኩል ማሳሳቢያ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ወንጀልን እንደ መደበኛ የንግድ ስራ በመያዝ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በመሆናቸው ክትትል ሲደረግባቸው መቆየቱን አገልግሎቱ ለኢዜአ ገልጿል፡፡
በዚህ መሠረትም ክትትል ተደርጎ የተደረሰባቸው እና በሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ላይ የተሰማሩ 138 ዋነኛ ተጠርጣሪዎች የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲታገድ ተደርጓል ነው ያለው፡፡