Fana: At a Speed of Life!

ከዩናይትድ መሰናበት እስከ ባሎንዶር ዕጩነት – ስኮት ማክቶሚናይ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ስኮትላዳዊው የቀድሞ የማንቼስተር ዩናይትድ የመሀል ሜዳ ተጫዋች ስኮት ማክቶሚናይ ከቀያይ ሰይጣኖቹ ጋር ከተለያየ በኋላ ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል፡፡

ተጫዋቹ ባለፈው ክረምት ናፖሊን በተቀላቀለ በመጀመሪያ ዓመቱ የስኩዴቶውን ዋንጫ ከክለቡ ጋር ከማንሳት አልፎ በጣልያን ሴሪ አ የውድድር ዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል፡፡

ከዩናይትድ ጋር ከተለያየ በኋላ በጣልያን እንደገና የተወለደው ስኮት ማክቶሚናይ በናፖሊ የራሳቸውን ደማቅ ታሪክ ከሰሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡

ማክቶሚናይ ማንቼስተር ዩናይትድ በ2016/17 የውድድር ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ከአርሰናል ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ ተቀይሮ በመግባት ነበር ለዩናይትድ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው፡፡

የማንቼስተር ዩናይትድ አካዳሚ ፍሬ የሆነው ማክቶሚናይ በርካታ አሰልጣኞች ሲቀያየሩ በነበረበት ቡድን ውስጥ ራሱን ለማሳየት የሚተጋ ተጫዋች እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ የአሰልጣኝነት ዘመን በ25 ነጥብ 7 ሚሊየን ፓውንድ ነበር ዩናይትድን በመልቀቅ የጣልያኑን ክለብ ናፖሊን የተቀላቀለው፡፡

በኔፕልሱ ክለብ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች በመሆን በክለቡ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ ለመግባት ጊዜ ያልፈጀበት ስኮቲሹ አማካይ፥ ለተጠራጠሩት ብቃቱን በሚገባ አሳይቷል፡፡

የልጅነት ክለቡ ማንቼስተር ዩናይትድ በሊጉ 15ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ማክቶሚናይ በአንጻሩ በዋንጫ የታጀበ ዓመት በማሳለፍ በኔፕልስ ሕልሙን እየኖረ ይገኛል፡፡

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የሴሪ አ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ከመመረጥ አልፎ ለባሎንዶር ሽልማት ከታጩ የመጨረሻ 30 ዕጩ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ መካተት የቻለበትን አስደናቂ ዓመት አሳልፏል፡፡

በሴሪ አ የመጨረሻ ጨዋታ የውድድር ዓመቱን ስኬታማ ጊዜ የሚያስታውስ አስደናቂ የመቀስ ምት ግብ በማስቆጠር ናፖሊን ወደ ሻምፒዮንነት መምራቱ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በሴሪ ኤው 34 ጨዋታዎችን አድርጎ 12 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን ፥ በአንጻሩ በማንቼስተር ዩናይትድ በ178 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ያስቆጠረው 19 ግቦችን ብቻ ነው፡፡

በሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ ላንካስተር የተወለደው ስኮትላንዳዊው አማካይ ፥ ገና በአምስት ዓመቱ ነበር ማንቼስተር ዩናይትድን የተቀላቀለው።

አሁን በኔፕልስ ራሱን ያሳየው ስኮት ማክቶሚናይ በሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጪ ሕይወትን በደስታ መኖር ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡

ሕልም የሚመስለው የተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የማክቶሚናይ ስኬት በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን ማንቼስተር ዩናይትድ በሚገባ ሊጠቀመው ያልቻለው ብቃት እንዳለው ያሳየበት የውድድር ጊዜ ሆኖ አልፏል።

በወንድማገኝ ፀጋዬ

ፈጣንና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.