በአዋሽ ወንዝ ሙላት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ እንዲጠናከር ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች በአዋሽ ወንዝ ሙላት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ጥሪ አቀረበ።
ሰሞኑን በጣለው ከባድ ዝናብ በአዋሽ ወንዝ ሙላት ሳቢያ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የዳዎ፣ ኢሉና ሰበታ ሀዋስ ወረዳዎች እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀሬ፣ ኤጀርሳ ለፎና ወልመራ ወረዳዎች ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።
የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉና ሰበታ ሀዋስ ወረዳዎች በአዋሽ ወንዝ ሙላት ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ7 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የቢሮው ሃላፊ ሚሊዮን በቀለ (ኢ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥በአዋሽ ወንዝ ሙላት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በወንዙ ሙላት ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለይም ሕጻናትና ሴቶች አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት።
አሁን ላይ ችግሩን ለመቅረፍ በክልል ደረጃ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ፥ በቀጣይ ተጎጂዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።
የክልልና የፌዴራል መንግስታት እንዲሁም ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የወረዳዎቹ አስተዳዳሪዎች በበኩላቸው ፥በዘንድሮው ክረምት የአዋሽ ወንዝ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በመሙላቱ በርካታ ነዋሪዎች ለአስከፊ ችግር ተዳርገዋል ብለዋል።
ተፈናቃዮች በት/ ቤቶችና ሌሎች ቦታዎች በጊዜያዊነት ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቅሰው፥ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚፈልጉ አስገንዝበዋል።
ስለሆነም የሚመለከታቸው አካላት ምግብ ነክና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።
በመላኩ ገድፍ