Fana: At a Speed of Life!

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና ኦሜጋ ጋርመንት በትብብር ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና ኦሜጋ ጋርመንት በትብብር ለመስራት የጋራ ስምምነት አድርገዋል፡፡

በኹነቱ ላይ የሁለቱ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በጋራ ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በ13 የሬዲዮ ጣቢያዎች፣ በሁለት የቴሌቪዥን ቻናሎች እና በበርካታ የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች በሀገር ውስጥ እና በውጭ ቋንቋዎች በሚያሰራጫቸው የይዘት ስራዎች ተደራሽ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ እና ተመራጭ ሚዲያ መሆኑን የፋና ዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሸለመ ከቤ በስነስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

ተቋማችን በሰባት የሀገር ውስጥ እና በሁለት የውጭ ቋንቋዎች ተደራሽ ነው ያሉት አቶ ሸለመ ኦሜጋ ጋርመንት ከፋና ጋር በትብብር መስራቱ ትርፋማ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡

በፋና ዲጂታል ፖድካስት ‘ኤክስትራ ታይም’ የስፖርት ፕሮግራም ላይ የስፖርት አልባሳትን በማቅረብ በትብብር ለመስራት የወሰንነው ኦሜጋ ጋርመንት የፋናን ተደራሽነት እና ተወዳጅነት ከግንዛቤ አስገብቶ ነው ያሉት ደግሞ የኦሜጋ ጋርመንት መስራች እና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ብዙነህ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያን እናበሥራለን በሚል ተልዕኮ የሚሰራው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ መሆኑንም ገልጸዋል።

ስራ አስኪያጁ ፋና ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው፤ በፖድካስት አማራጭ መምጣቱ ደግሞ በዲጂታሉ ዓለም ይበልጥ ተደራሽነቱን እንደሚያሰፋው ተናግረዋል፡፡

የኦሜጋ ጋርመንት የማርኬቲንግ ማናጀር ዘውዱ ጥላሁን በበኩላቸው የፋና ፖድካስት በውስን ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ማትረፉ ምርታችንን ለዲጂታሉ ገበያ ለማስተዋወቅ ዕድል ሰጥቶናል ብለዋል፡፡

የፖድካስት አማራጭ በቀላሉ ተደራሽ በመሆኑ ለሰዎች ቀዳሚ ምርጫ እንዲሆን አድርጎታልም ነው ያሉት፡፡

በቀጣይ ምርቶቹን ወደ አሜሪካና አውሮፓ ገበያዎች ለማቅረብ የማስፋፊያ ስራ እየሰራ የሚገኘው ኦሜጋ ጋርመንት፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሲዳማ ቡና፣ ሃዋሳ ከተማ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ዲቻን ጨምሮ ለተለያዩ ክለቦች የስፖርት ትጥቅ እያቀረበ ይገኛል፡፡

በሀዋሳ ከተማ የሚገኘው ሀገር በቀሉ ኦሜጋ ጋርመንት ኩባንያ የተለያዩ የስፖርት ትጥቅ አምራች እና አቅራቢ ነው።

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.