ማንቼስተር ዩናይትድ ከአርሰናል …
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አዲሱ የውድድር ዘመን ገና በመጀመሪያው ሳምንት ሁለቱን የምንጊዜም ተቀናቃኞች ማንቼስተር ዩናይትድ እና አርሰናል አገናኝቷል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ጋር ከተራራቁ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡
ማንቼስተር ዩናይትድ ለመጨረሻ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ያሳካው በ2012/13 የውድድር ዘመን ሲሆን አርሰናል ደግሞ በ2003/04 የውድድር ዘመን እንደነበር ይታወሳል፡፡
ቡድኖቹ ምንም እንኳን ከሊጉ ዋንጫ ይራቁ እንጂ እርስ በርስ ሲገናኙ የሚያደርጉት የሜዳ ላይ ትንቅንቅ በስፖርቱ ቤተሰብ ዘንድ ይጠበቃል።
በሰር አሌክስ ፈርጉሰን እና አርሰን ቬንገር የአሰልጣኝነት ዘመን የማንቼስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ፉክክር ይበልጥ ትኩረት የሚስብ ነበር፡፡
ማንቼስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰንን ካጣ በኋላ በሊጉ ተፎካካሪ መሆን አቅቶት ዓመታትን አሳልፏል፡፡
አርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታን ካገኘ በኋላ ባለፉት ዓመታት የሊጉ ተፎካካሪ መሆን ቢችልም ለዓመታት የራቀውን ዋንጫ ማንሳት አልቻለም፡፡
በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በንቃት የተሳተፈው የሰሜን ለንደኑ ክለብ ቪክተር ዮኬሬሽ፣ ማርቲን ዙቢሜንዲ፣ ክርስቲያን ኖርጋርድ፣ ክርስቲያን ሞስኬራ፣ ኖኒ ማዱኬ እና ኬፓ አሪዛባላጋን ወደ ስብስቡ በመቀላቀል ይበልጥ ተጠናክሯል፡፡
በ2024/25 ደካማ የውድድር ዓመት ያሳለፈው ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ ቤንጃሚን ሼሽኮ፣ ማቲያስ ኩና፣ ብሪያን ምቤሞን እና ዲዮጎ ሊዮንን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡
ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት 2ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አርሰናል በ2025/26 የውድድር ዓመት የሊጉን ዋንጫ ያሳካሉ ተብለው ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች መካከል አንዱ ነው፡፡
አርሰናል ከዚህ ቀደም በሊጉ ለተከታታይ 3 ዓመታት 2ኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀ በኋላ በ4ኛው የውድድር ዓመት ዋንጫውን ማንሳቱ የሚታወስ ሲሆን ወቅቱም 2001/02 ነበር፡፡
የዘ አትሌቲክስ ፀሃፊዎች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ግምታቸውን ሲያስቀምጡ አርሰናል 2ኛ ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ 8ኛ ደረጃን ይዘው እንደሚያጠናቅቁ ተንብየዋል።
የቀድሞ የማንችስተር ሲቲ ተጫዋች ሚካ ሪቻርድስ የዛሬ ተጋጣሚዎችን የውድድር ዓመት ቅድመ ግምቱን ሲያስቀምጥ አርሰናል እንደ አምናው ተፎካካሪ ይሆናል ዋንጫውን ግን አያሸንፍም፤ ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ እስከ 6ኛ ባለው ደረጃ የውድድር ዓመቱን ያጠናቅቃል ብሏል።
የቀድሞ የማንቼስተር ዩናይትድ ኮከብ ዋይን ሩኒ አርሰናል በድጋሚ 2ኛ እንዲሁም ማንቼስተር ዩናይትድ እስከ 5ኛ ባለው ደረጃ የውድድር ዓመቱን ያጠናቅቃሉ ሲል፤ የምንጊዜም የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ አለን ሺረር በበኩሉ አርሰናል 2ኛ ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ 6ኛ ደረጃን ይዘው ይጨርሳሉ ነው ያለው።
የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ዛሬ በኦልድትራፎርድ ከሚደረገው የአርሰናል ጨዋታ በፊት ተቃውሞ ለማሰማት አስበው የነበረ ቢሆንም ተቃውሞውን ለጊዜው መሰረዛቸውን ገልጸዋል።
ማንቼስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ 22 የመክፈቻ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ከሁሉም ቡድኖች የተሻለ ሲሆን ዛሬ ይህንን ሪከርዱን ያስቀጥል ይሆን የሚለው ይጠበቃል፡፡
ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት ከ30 የሚደረገውን የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ሲሞን ሁፐር በመሐል ዳኝነት እንዲሁም ፖል ቴርኒ በቫር ዳኝነት ይመሩታል።
በወንድማገኝ ፀጋዬ