Fana: At a Speed of Life!

በተጠባቂ ጨዋታዎች ዛሬ የሚመለሰው ፕሪሚየር ሊጉ…

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከወራት በኋላ በአዲስ የውድድር ዘመን ባለፈው ሳምንት ጅማሮውን ያደረገው ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ ግብር ዛሬ ይጀምራል።

ዛሬ ምሽት በለንደን ደርቢ የኢንዞ ማሬስካው ቼልሲ ዌስትሃም ዩናይትድን ከሜዳው ውጭ ይገጥማል።

ምሽት 4:00 በሚጀምረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የዌስትሃሙ አሰልጣኝ ግራሃም ፖተር የቀድሞ ክለባቸውን በተቃራኒ ይገጥማሉ።

በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ ግብር በአዲስ አዳጊው ሰንደርላንድ የ3 ለ ዐ ሽንፈት ያስተናገደው ባለሜዳው ክለብ ዌስትሃም የመጀመሪያውን ነጥብ ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባል።

በሌላ የለንደን ደርቢ ከክሪስታል ፓላስ ጋር ነጥብ በመጋራት ሊጉን በአቻ ውጤት የጀመሩት ቼልሲዎች የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት በሚያደርጉት ጨዋታ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

ፕሪሚየር ሊጉ ነገ ቀጥሎ ሲደረግ፥ ማንቼስተር ሲቲን ከቶተንሃም ሆትስፐር የሚያገናኘው መርሐ ግብር ከፍተኛ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ሲቲ ዎልቭስን 4 ለ ዐ እንዲሁም ቶተንሃም አዲስ አዳጊውን በርንሌይ 3 ለ ዐ መርታት ችለዋል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ነገ 8:30 በኢትሃድ ይደረጋል።

በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ማንቼስተር ዩናይትድን በመርታት ውድድሩን በድል የጀመረው አርሰናል ነገ ምሽት አዲስ አዳጊውን ሊድስ ዩናይትድ በሜዳው ያስተናግዳል።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ ከሊድስ ጋር ባደረጋቸው ያለፉት አምስት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ሁሉንም ማሸነፍ የቻለ ሲሆን፥ በነገውም ጨዋታ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል።

ከሁለት ዓመት የሻምፒየንሺፑ ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተመለሱት ሊድስ ዩናይትዶች ኤቨርተንን በማሸነፍ ሊጉን በድል መጀመራቸው ይታወሳል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ነገ ምሽት 1:30 ይደረጋል።

ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ቦርንማውዝ ከዎልቭስ፣ ብሬንትፎርድ ከአስቶን ቪላ እንዲሁም አዲስ አዳጊዎቹ ሰንደርላንድ ከበርንሌይ በተመሳሳይ 11 ሰዓት የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።

ከአስከፊ የውድድር አመት በኋላ ሊጉን በሽንፈት የጀመሩት ማንቼስተር ዩናይትዶች የውድድር አመቱን የመጀመሪያ ድል እያለሙ እሁድ ምሽት 12:30 በክራቨን ኮቴጅ ፉልሃምን ይገጥማሉ።

በአርሰናል ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያስመለከቱት ዩናይትዶች በእሁዱ ጨዋታ ለአሸናፊነት ቅድመ ግምት አግኝተዋል።

በሌሎች የእለቱ መርሐ ግብሮች ክሪስታል ፓላስ ከኖቲንግሃም ፎረስት እንዲሁም ኤቨርተን ከብራይተን ቀን 10 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የፕሪሚየር ሊጉ የ2ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሰኞ ምሽት 4:00 ኒውካስል ዩናይትድ ከሊቨርፑል በሚያደርጉት ጨዋታ ይቋጫል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከሜዳ ላይ ፉክክር ባለፈ በኒውካስል ዩናይትዱ የፊት መስመር ተጫዋች አሌክሳንደር ኢሳክ ምክንያት ተጠባቂ ሆኗል።

ሊቨርፑልን ለመቀላቀል በመፈለግ ከኒውካስል ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባው ተጫዋቹ በሰኞ ምሽቱ የጀምስ ፓርክ ፍልሚያ ለክለቡ ግልጋሎት አይሰጥም።

በሃይለማርያም ተገኝ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.