በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የገበያ ማረጋጋት ሥራ…
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀጣይ ለሚከበሩ በዓላት ምርቶችን በስፋት በማቅረብ የገበያ ማረጋጋት ሥራ እየተከናወነ ነው ፡፡
የከተማዋ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በሰጡት መግለጫ ፥ በቀጣይ ለሚከበሩ በዓላት መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ለሕብረተሰቡ በስፋት ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የፍጆታ ምርቶችን በብዛትና በጥራት በማቅረብና ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ በማድረግ የገበያ ማረጋጋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በመዲናዋ መግቢያ በሮች የተገነቡ አምስት ሁለገብ የግብርና ማዕከላት ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የግብርና ምርቶችን በቀጥታ በማቅረብ የሕገ ወጥ ደላላን ሚና ቀንሰዋል ነው ያሉት፡፡
በማዕከላቱ ከ500 በላይ ነጋዴዎች እና ከ250 በላይ አምራቾች ምርታቸውን በብዛትና በጥራት እያቀረቡ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከደመወዝ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በየደረጃው ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሕገ ወጥ ነጋዴዎች በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉም ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በመራኦል ከድር