ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹን ቁጥር 88 ሚሊየን ለማድረስ አቅዷል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ያሉትን 83 ነጥብ 2 ሚሊየን ደንበኞች ቁጥር በተያዘው በጀት ዓመት 88 ሚሊየን ለማድረስ አቅዷል።
ተቋሙ የ3 ዓመታት ቀጣዩ አድማሥ ስትራቴጅ እና የ2018 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅዱን ዛሬ አስተዋውቋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንዳሉት፤ ስትራቴጂው የሀገሪቱን የ10 ዓመት ዕቅድ መሠረተ ያደረጉ ስራዎችን ለመስራት ያለመ ነው::
ዕቅዱ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕድገትና ስትራቴጂ ታሣቢ ያደረገ አሻጋሪ ዕቅድ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ሀገርን በዲጂታል ዘርፍ በጉልህ በማስታጠቅ ከዓለም ጋር ተወዳዳሪ በመሆን የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ይሰራል ብለዋል።
ስትራቴጂው ከገበያና ከሳይበር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ተግዳሮቶችን ለመፍታትም ታቅዶ የተበሰረ መሆኑን ገልጸዋል።
በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት በከተማ 1 ሺህ 228 እና በገጠር 322 ጣቢያዎች ተደራሽ እንደሚሆኑ አንስተው፤ በተያዘው በጀት ዓመት በ10 ከተሞች የ5G ኔትወርክ ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት።
ተቋሙ ያሉትን 83 ነጥብ 2 ሚሊየን ደንበኞች በ2018 በጀት ዓመት በስድስት በመቶ በማሳደግ 88 ሚሊየን ለማድረስና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቆየት ግብ ማስቀመጡን ጠቁመዋል።
የቴሌብር ትራንዛክሽኑን 4 ነጥብ 43 ትሪሊየን ብር ለማድረስ ማቀዱንም ተናግረዋል።
ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 235 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለማግኘት ግብ አስቀምጧል ነው ያሉት::
በቀጣይ ሶስት ዓመታት ስትራቴጂ 112 ነጥብ 4 ሚሊየን ተጠቃሚ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው ገመድ አልባ ኔትወርክ ለመዘርጋት ታስቦ እየተሰራ እንደሚገኝ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ጠቁመዋል።
በሰማኸኝ ንጋቱ