Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ፀሐይ !

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፀሐይ ከአድማሷ ግርጌ የምስራቁን መርጣ ብሩህ መልኳን የምትገልጠው ከዚሁ ከአድዋ ተራራ እና ከጉባ ሸለቆ ይመስላል።

በርግጥ ከምድሯ ማህጸን ያልተነካው ፀጋዋን የምድርን ሚዛን ባሳቱ ቅኝ ገዥዎች ‘የአባት ዕዳ ለልጅ ይሉት’ ዓይነት ዝንቅ ውሎች የቻሉትን ያህል አህጉሪቱን እንደ ለፋ ቆዳ ሊያደርጓት ደክመዋል።

ዋ ! ….ያቺ ዓድዋ !

የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ግጥም እዚህ ጋር ርዕሱ ብቻ በቂ ይሆናል። ለአፍሪካ የነጻነት ፀሀይን ፈንጥቆ ፣ የተገዥነት ሸምቀቆን በጣጥሶ ጥሏል።

ከአድዋ ተራራ የወጣችው ፀሀይ በኬፕ ታውን የምትጠልቅ የጀንበር ውበትን ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን በአሸናፊነት አስመልክታለች።

ዛሬም ድረስ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ቀና ብለው ፣ አንገታቸውን እየነቀነቁ ከሚያዜሙት ብሔራዊ መዝሙራቸው ፊት በሚመለከቱት ሰንደቅ ላይ የዓድዋ ጀግኖች አባቶች የደም ቀለምን ማየታቸው እርግጥ ነው።

ኢትዮጵያዊያን ያ መንፈስ አልለቀቃቸውም።

ያ ቀና ማለት በደምስሮቻቸው ወደ ልጆቻቸው ፣ ወደ ጉባው ሸለቆ ወስዶ እንደጅራፍ ዓባይ ላይ አጋምዷቸዋል።

ህዝቦቿ እንደ ወንዙ ገባሮች የህብረታቸው በደማቅ መሃላ አትመው በእምቢ ለሀገሬ ወኔ ፣ ‘ እሳት እሳትን ወለደ’ ይባሉ ዘንዳ የግድቡ ዋልታ እና ማገር ሆነው በፅናት ቆመዋል።

የቀለም ቀንድ ይሏቸዋል ነበር። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ።

ወራሪው ሀይል ከኢትዮጵያ ወጥቶ ከሄደ በኋላ ኢትዮጲያዊያን የነበራቸው ኩራትና ክብር በይፋ ይታይ ነበር።ከልጅ እስከ ደቂቅ አንገቱን ከፍ አድርጎ በየትም ቦታ እና ጊዜ ኩራትና ክብሩን ይጠበቅ ነበር ብለው ጽፈዋል።

ያ ኩራት እና ክብር በዳግማዊ ዓድዋ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የምረቃት ድግስ ለሁሉም ሲበሰር ልባቸው ነዝሯል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ዛሬም እንደትናንቱ ደማቋን የፀሃይ ግርማ ሞገስን ከራባት እስከ ፍሪታወን ፣ ከጅቡቲ እስከ ኬፕታውን ፣ ከአንተናናሪቮ እስከ ሉሳካ ድረስ መላው አፍሪካውያን በራስ አቅም ግዙፍ ፕሮጀክትን ጀምሮ መጨረስ ህልማዊ ሳይሆን ዕውናዊ መሆኑን እነሆ ህያው ማሳያ ከኢትዮጵያ ለአፍሪካ።

አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷ ፣ የፈጣሪ በረከቷ እርግማን ሆኖ ዜጎቿ ማዕድናቱን ለማውጣት ዶማ እና አካፋን ከመጨበጥ ይልቅ  ጠብመንጃ ማንሳት የሰርክ ተግባራቸው እንዲሆን ተሰርቶባቸዋል።

ሰላም እና ልማት በራስ አቅም የተፈጥሮ ሀብትን አልምቶ ከድህነት ለመውጣት ግን የአንችልም ልጓሙ በዜጎቿ ላይ ጠብቋል።

እውነታው ግን የምድሪቱ 30 በመቶ ማዕድን የእኛው ነው።

ደቡብ አፍሪካ ፣ ጋና ፣ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ ብትረግጡት ወርቅ ነው የሚባል ምድር ላይ ናቸው። አለም ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ ለመስራት ኮባልት ፍለጋ የምድሪቱን 60 በመቶ ከተሰጣት ኮንጎ ደጅ ላይ መጥናት እንጂ ግጭት መጥራት አይጠበቅበትም።

ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኀን ”የቅድመ ጠቢባን አዋይ ፣ ዓባይ የምድር ዓለም ሲሳይ ” ያሉት ወንዝ የሩቅ የቅርቡን ለጋራ ልማት የሚጠራ ግድብ ተሰርቶለታል። ይህ የአፍሪካ ግዙፉ ግድብ ለአፍሪካዊያን በራስ አቅም የራስን ሀብት ለማልማት መስፈንጠሪያቸው ነው።

ፓን አፍሪካኒስቱ ፕሮፌሰር ፓትሪስ ሎች ሉሙምባ በፈረንጆቹ 2018 በአፍሪካ ህብረት የጸረ ሙስና ጉባሄ ላይ ያደረጉት ንግግር አይረሴ ነው።

“Africa is not poor; we are robbed. Our minerals our mind, our oil is pumped, and our wealth is shipped abroad while we beg for aid.”

አፍሪካ ደሃ አይደለችም፤ ማዕድናቶቻችን ወጥተዋል ፣ ነዳጃችን ይፈሳል ፣ ሀብታችን ወደ ውጭ ተልኳል፣ እኛ ግን ለእርዳታ እየለመንን ነው።” ማለታቸውን ስናስታውስ የተፈጥሮ ሀብቷ ላይ የምታተኩር አፍሪካ ነገዋን ብሩህ ለማድረግ አትፈተንም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ’መደመር’ መፅሃፋቸው ላይ የሆብስ ወጥመድ ያሉት የሊቃውንት አባባል እዚህ ጋር ይመጣል።

የሆብስ ወጥመድ ማለት አንዱ አንዱን እየፈራና ቂም ቂምን እየወለደ ያለበቂ ምክንያት ግጭት እና ለደም መፋሰስ አዙሪት መዳረግ ማለት ነው።

አፍሪካም የሆብስ ወጥመዷን አሽቀንጥራ ለመጣል የኢትዮጵያዊያን ያለ ልዩነት የቆሙበት ሀውልት ሰሪ ጠንቅቆ የቀረጸው የመሰለው የማይናወጥ የጉባ በረሃ ጽናታቸው አስረጂ ይሆናታል።

አፍሪካን በሀይል የማስተሳሰር ጅምሯን በጎረቤቶቿ የጀመረች ኢትዮጵያ ግዙፍ ግድብ ጀምሮ የመጨረስ ልምዷን በአዲስ ዓመት ለተቀረው አፍሪካ ፤ የፀሐይ ወጋገኗን በመፈንጠቅ የአፍሪካ ፀሐይም ሆናለች።

በኃይለኢየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.