ጋዜጠኛና ደራሲ የምወድሽ በቀለ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጋዜጠኛ እና ደራሲ የምወድሽ በቀለ ፣በድርሰትና በስነ ግጥም እንዲሁም በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎቿ ሀገሯን አገልግላለች፡፡
ጋዜጠኛ የምወድሽ በቀለ ከእናቷ ወ/ሮ ወርቅነሽ ወልደማሪያም እና ከአባቷ ሻምበል ባሻ በቀለ ወ/ገብርኤል ነሐሴ 19 1952 ዓ.ም ነበር የተወለደችው።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በአፍሪካ አንድነት ትምህርትቤት፤ 2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በአዲስ ከተማ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትላለች።
የምወድሽ፣ እጅግ በጣም ጎበዝ ተማሪ ፣በትንሽ ነገር ስቃ ተማሪን የምታስቅ ነበረች።
ግጥም መጻፍ የጀመረችበት አጋጣሚ በትምህርት ቤት የሚያበሽቋትን ለማብሸቅ ስትል እንደነበር ይነገራል።
የስነጽሑፍ ስራዋን በአደባባይ መስራት የጀመረችው ጌታቸው ተካልኝ በሚያሳትመው ፀደይ መጽሔት ላይ አርቲክሎችን በመጻፍ እና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በፍሪላንስ በመጻፍ ነበር ።
ወደ ግቧ የሚያደርሳት ሌላኛው ክስተት ደግሞ ባህልና ቱሪዝም ባዘጋጀው የጽሑፍ ውድድር ላይ በመሳተፍ አሸንፋ የመጀመሪያ የግጥም መጽሐፏን በ 1972 ዓ.ም አብዮታዊ ግጥሞች ብለው በማጭድና መዶሻ አጅበው አሳትመውላት ነበር።
የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማሕበርን ለረጅም አመታት በፕሬዚዳንትነት የመራችው ጋዜጠኛዋ የኢትዮጵያ ሴቶች ማሕበራት የቦርድ ሰብሳሰቢ በመሆንም አገልግላለች።
ሴቶች ይችላሉ (Women can do it) የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት መስራችና ዋና ዳይሬክተር የነበረች ስትሆን በተጨማሪም እጅግ በርካታ የበጎ ስራ ማሕበራት ውስጥ መስራችና አመራር በመሆን ስታገለግል ኖራለች።
በአሐዱ ሬዲዮ ላይ ከምወድሽ ገፆች የተሰኘ በሴቶች ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ እንዲሁም በአሻም ቴሌቪዥን የሚተላለፍ የምወድሽ ገፆች አዘጋጅም ነበረች።
በሕይወት ዘመኗ ባበረከተቻቸው አስተዋፅኦዎች በርካታ ሽልማቶችን ያገኘችው ጋዜጠኛዋ፣ የ2016 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማትን ጨምሮ ሌሎችን እውቅና እና ሽልማቶች አግኝታለች።
ሳቂታዋ በሲቪል መርማሪ ፖሊስ በርካታ አሰቃቂና ዘግናኝ የወንጀል ማህደሮችን በአደባባይ ያጋለጠች፣ ለዘመናት ተቀብረው የቆዩ ዶሴዎችን አነፍንፋ ያወጣች ፣ ለበርካታ ወንጀሎች ሕጋዊ ፍትሕ እንዲያገኙ የተጋች እንስት ነበረች፡፡
የብዙ አቅመ ደካሞች ጧሪ እና ደጋፊ የነበረችው ደራሲ እና ጋዜጠኛዋ የምወድሽ በቀለ ለአጭር ጊዜ ባጋጠማት ሕመም በሕክምና ስትረዳ ቆይታ ነሐሴ 23 ቀን ሌሊት አርፋለች፡፡
በዛሬው እለትም ወዳጅ ዘመዶቿ እና የሙያ አጋሮቿ በተገኙበት የታላቋ ጋዜጠኛና ደራሲ የምወድሽ በቀለ የቀብር ሥነሥርዓት አየር ጤና በሚገኘው ኪዳነምህረት ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።