Fana: At a Speed of Life!

የነብዩ መሀመድ ልደትን ስናከብር እሳቸው ይመክሯቸው የነበሩትን እሴቶች ማሰብ ይገባል – ሼህ አብዱል ሃሚድ አህመድ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የነብዩ መሀመድ ልደትን ስናከብር እሳቸው ይመክሯቸው የነበሩ የሰላም፣ የመቻቻል፣ የመከባበር እና የአንድነት እሴቶችን ማስታወስ ይገባል አሉ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ አባል ሼህ አብዱል ሃሚድ አህመድ።

1 ሺህ 500ኛው የነቢዩ መሀመድ (ሰዐወ) የልደት በዓል የፊታችን ሐሙስ ነሐሴ 29 ቀን 2017 ዓ.ም በአንዋር መስጂድ የእምነቱ ተከታዮች እና የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት ይከበራል።

ሼህ አብዱል ሃሚድ አህመድ በዓሉን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ የሃይማኖት ጽንፈኝነትና አለመቻቻል እየበረታ ባለበት በዚህ ዘመን የታላቁን ነቢይ ህያው አስተምህሮ መከባበር እና መግባባት በሰላም አብሮ የመኖር መሰረት መሆኑን ያስታውሰናል ብለዋል።

ታላቁ ነቢይ ጎረቤቱ እየተራበ ጠግቦ ያደረ እርሱ አማኝ አይደለም ማለታቸው የርህራሄን አስፈላጊነት ከማጉላት ባሻገር፤ ሙስሊሞች ለሌሎች እንዲያዝኑና አክብሮት እንዲቸሩ ያስተምራል ነው ያሉት።

እንደ ሙስሊም ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፤ በተለይም በክፍፍልና በግጭት ጊዜ ተመሳሳይ የመቻቻልና የመከባበር እሴቶችን እንድናጎላ ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ ቡድንተኝነትን፣ የፖለቲካ ግጭትንና ማህበራዊ አለመግባባቶችን ጨምሮ የተለያዩ ተግዳሮቶችን በተጋፈጠበት በዛሬው ዘመን፣ ከግል ወይም ከጎሳ ጥቅም ይልቅ የህዝበ ሙስሊምን ጥቅም በማስቀደም ከልዩነቶች ተላቀን ለጋራ ጥቅም እንድንረባረብ የነቢዩ መሐመድ አስተምህሮ ይጎተጉተናል ነው ያሉት።

የነብዩ መሀመድን ልደት ስናከብር እርሳቸው ይመክሯቸው የነበሩትን የሰላምን፣ መቻቻልን፣ ከሌሎች ጋር ተከባብሮ የመኖር እና የአንድነት እሴቶችን ልናስታውስ ግድ ይላል ሲሉም አሳስበዋል።

በዕለት ተለት ህይወታችን የእርሳቸውን ፈለግ ተግባራዊ ለማድረግ መትጋት እንዲሁም ፍትህ ለሰፈነበት ዓለም እውን መሆን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የታላቁ ነቢይ መወለድ ለሰው ልጆች የብርሃን ብስራት የተበሰረበት መሆኑን በማሰብ፣ በጥልቅ ስሜት የምንደሰትበት፣ ስማቸውን አብዝተን የምናወድስበትና ውዴታና ሰላምታ የምናቀርብበት ጊዜ ነው ብለዋል።

ወሩ እና ይህ ዕለት ዘመን የማይሽረው ነቢያዊ ተልዕኳቸውን፣ አስተምህሯቸውንና የህይወት ምሳሌነታቸው ያቀፋቸው እሴቶቻቸውን የምናሰላስልበት ትልቅ አጋጣሚ ነው ሲሉም በመግለጫው አንስተዋል።

በመሆኑም በዓሉ በመረዳዳት እና በመተሳሰብ ሊከበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመሳፍንት እያዩ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.