ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ የሞተ እንደማስነሳት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ተጀምሮ የኋሊት የሄደውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማጠናቀቅ የሞተ እንደማስነሳት ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የጉባ ላይ ወግ” በተሰኘ ልዩ ቃለ ምልልስ ላይ ባደረጉት ቆይታ፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ደም እና ላብ ጠብ አድርገን የውሃን ጠብታ ለቁምነገር ያዋልንበት ሥፍራ ነው ብለዋል፡፡
ትናንሽ እሳቤ ያላቸው ሰዎች ሀገራዊ ጥቅምን ባለመገንዘብ ለተላኩላቸው አካላት ፍላጎታቸውን ያሳኩ መስሏቸው ብዙ ሙከራዎች እንዳደረጉ አስታውሰዋል፡፡
ግድቡ ለብዙ ጊዜያት የነበረ በደል፣ ጥፋትና የድህነት ቀንበር የሚሰብር ትዕምርታዊ ፕሮጀክት ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡፡
ግድቡ ከአሁን ቀደም ጀምረን ካሳካናቸው አረንጓዴ አሻራ እና የኮሪደር ልማትን ከመሳሰሉ ፕሮጀክቶች የተለየ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ የተጀመረን መጨረስና ተጀምሮ የኋሊት የሄደውን ማጠናቀቅ ለየቅል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
መስተካከል ያለባቸውን አፍርሶ ዳግም ለመስራትና ቀሪ ሥራዎችን ለማከናወን የጠየቀው ገንዘብና የነበሩት ጂኦፖለቲካዊ ጫናዎች ፕሮጀክቱ የኋሊት ሲሄድ እንደነበር ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ነገር ግን በፈጣሪ እርዳታ፣ በአቅምና አቋም ድማሮ፣ በሕዝባችን ቁርጠኝነትና ለዓመታት በአስቸጋሪ መልክዓ ምድር ውስጥ ሲሰሩ በነበሩ ሰራተኞች ትጋት ለፍጻሜ በቅቷል ነው ያሉት፡፡
የባንዳ እና የባዳ ትስስር የኢትዮጵያውያንን ሕልሞች ሲያጨናግፉ መቆየታቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ አሁን አሁን ከዓለም ፍትህን የመጠበቅ ዝንባሌ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የዘመናት በደልና ጥፋትን የሚያስቆምና የሚያስቀር እንዲሁም ለብዙ ጊዜያት የነበረን የድህነት ቀንበር የሚሰብር ትዕምርታዊ ፕሮጀክት እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
ያለፍንበትን ፈተና እና የተሰራውን ስራ በቀላል መንገድ መረዳት የሚፈልጉ አካላት ኢትዮጵያ እና ካርቱምን በማየት መገንዘብ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ጦርነት አዲስ ሥራን ለመስራት የማያስችልና የተገነባን ሀገር የሚያፈርስ መሆኑን ገልጸው ፥ ለአብነትም ካርቱም በተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭት ዳግም ለመገንባት በማይቻልበት ደረጃ መፍረሷን ጠቅሰዋል፡፡
ያለፍንባቸው ፈተናዎች የግድቡን ግንባታ ለማስቆም በቂ ምክንያቶች ነበሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ ነገር ግን ባንዳዎች ሥራችንን እንዳያቆሙ እየተከላከልን ግድቡ አንድም ቀን እንዳይቋረጥ ክትትል በማድረግ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓታችንና ዕይታችን በመቀየሩ የጀመርነውን ለፍሬ የማብቃት ሥር የሰደደ ቁርጠኝነት ስላለን አድካሚና አሰልቺ ቢሆንም ተወጥተነዋል ብለዋል፡፡
የታሪክ ተመራማሪዎችና ምሁራን ከፖለቲካ ወገንተኝነት የግድቡን ሒደት ከመሰረቱ አጥንተው ቢጽፉት ለትውልድ ብዙ ትምህርት እንደሚገኝበትም ጠቁመዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ